ለቅዱስ ቁርባን ስለ መዘጋጀት

                                                                                   በአዜብ ገብሩ
ልጆች ዛሬ ቅዳሴ ስናስቀድስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ምን ማድረግ እንዳለብን እነግራችኋለሁ፡፡
በቤተክርስቲያን ጸሎት እናደርጋለን፣ እንቆርባለን፣ ትምህርት እንማራለን፡ስናስቀድስ ከእግዚአብሔር፣ከመላእክት እና ከቅዱሳን ጋር ሰለምንገናኝ ማስቀደስ በጣም ደስ ይላል፡፡

ልጆች ልንቆርብ ስንል ምን ማድረግ እንዳለብን ታውቃላችሁ? የሠራነው ኃጢአት ካለ ለእግዚአብሔር እና ለንስሐ አባታችን መናገር አለብን፡፡ የተጣላነው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅ፣ ውሸት አለመዋሸት አለብን፡፡ ሌላው ልጆች ገላችንን መታጠብና ንጹሕ የሆነ ልብስ መልበስ አለብን፡፡

ምክንያቱም ከሁሉም በላይ የሆነውን የአምላክ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ልንቀበል ስለሆነ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነውን ልብሳችሁን ከለበሳችሁ በኋላ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት በቤተክርስቲያን መገኘት አለባችሁ፡፡ ይህንንም ለወላጆቻችሁ ነግራችሁ በጊዜ ይዘዋችሁ እንዲመጡ አድርጉ፡፡ በቅዳሴ ጊዜም እግዚአብሔር የማይወደውን ወሬ ማውራት ስለማይፈቀድ ይህን ማድረግ የለባችሁም ዝም ብላችሁ ቅዳሴውን መከታተል አለባችሁ፡፡ ከጎናችሁ የቆሙ ሕፃናትም ሲያወሩ ካያችሁ ክቡር በሆነው በእግዚአብሔር ቤት እንዳሉ ልትነግሯቸው ይገባል፡፡

የቅዳሴ ሥርዓት እና ምንባብ ያለበት መጽሐፍ ይዛችሁ ጸሎቱን በደንብ መከታተል አለባችሁ፡፡ልትቆርቡም ስትሉ ከጎናችሁ ካለው ልጅ ጋር መጋፋት መሰዳደብና መጣላት አይገባም፤ ተራችሁን በትህትና ቆማችሁ መጠበቅ አለባችሁ፡፡ ከቆረባችሁ በኋላ የቅዳሴ ጸበል ጠጡ፡፡ ቆሻሻ የሆነ ነገር ወደ አፋችሁ እንዳይገባ፣ከአፋችሁ እና ከአፍንጫችሁም ምንም ዓይነት ነገር እንዳይወጣ አፋችሁን በነጠላችሁ ሸፍኑ፡፡ ቅዳሴው አልቆ ዲያቆኑ በሰላም ወደየቤታችሁ ግቡ ብሎ እስኪያሰናብት ድረስ በቤተክርስቲያን ቆዩ፤ቅዳሴው ሲጠናቀቅም እግዚአብሔርን አመስግናችሁ በመንገድ እንቅፋት እንዳይመታችሁ እየተጠነቀቃችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር ወደየቤታችሁ ሂዱ፡፡

እኛ ቤተ ክርስቲያን ሄደን ስንቆርብ ጌታችንም ከእኛ ጋር ወደ ቤታችን ይመጣል፤በዚህም ምክንያት ቤታችን ይገባል፤ቤታችንንም ይባርክልናል፡፡