‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› – ክፍል አንድ

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ለሦስት ጊዜ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያው ፋሲካ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበትና በቤተ መቅደስ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት ሲኾን፣ በመጨረሻው የፋሲካ ሰሙንም እንደዚሁ ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደሱን አንጽቶ ጌታችን በፋሲካው ማግስት ተሰቅሏል፡፡ በሁለቱ ፋሲካዎች መካከል በነበረው ፋሲካ ነው ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ የመጣው፡፡ ቤተ ሳይዳ የመጠመቂያው ሥፍራ ስም ሲኾን ከአጠገቡ ደግሞ የበጎች በር ነበር፡፡ (የበጎች በር በአሁኑ ሰዓት የቅዱስ እስጢፋኖስ በር እና የአንበሳ በር ተብሎ ይጠራል)፡፡

እንደሚታወቀው ዘመነ ኦሪት በግ መሥዋዕት ኾኖ የሚቀርብበት ዘመን ነበር፡፡ መሥዋዕት ኾነው የሚቀርቡ በጎች የሚገቡት በዚህ በር ነበር፡፡ በሩ በጎቹ ነውር እንደሌለባቸው ማለትም ቀንዳቸው እንዳልከረከረ፣ ጥፍራቸው እንዳልዘረዘረ፣ ፀጕራቸው እንዳላረረ የሚጠኑበት፤ የአንድ ዓመት ተባዕት (ወንድ) መኾናቸው የሚታይበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህን መሥፈርት አሟልተው ያለፉ በጎች ለመሥዋዕትነት ሲቀርቡ ለዚህ ብቁ ያልኾኑትን ግን ለይተው፣ በአለንጋ እየገረፉ ያስወጡአቸዋል፡፡

በቤተ ሳይዳ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያዪቱ ወርዶ ውኃውን አንዳንድ ጊዜ ያናውጠው ነበር፡፡ ይህ መልአክ በሰው ቍስል፣ በበሽታም ዅሉ ላይ የተሾመ የስሙ ትርጓሜም ‹‹እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው›› ማለት የኾነ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ መልአኩ ውኆችን ለመቀደስ፣ ጸሎትን ከሰው ወደ ፈጣሪ ለማድረስ ወደ ውኃው ይወርድ ነበር፡፡ ይህም በየትኛውም ውኃ መዳን ባይቻለንም ቅዱሳን መላእክት የነኩት ውኃ በረከትና ፈውስ እንደሚያሰጥ የሚያስረዳ ነው፡፡ ውኃው ከተነዋወጠ በኋላ ከደዌው መዳን የሚችለው በመጀመሪያ የሚገባ በሽተኛ ነበር፡፡ በዚህ የጠበል ሥፍራ በነበሩ አምስት መመላለሻዎች በሽተኞች በተለይ አንካሶች፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር፡፡

ከሌሎች በሽተኞች በተለየ እነዚህ የውኃውን መናወጥ አይተው ለመግባት፣ በዓይናቸውም ለማየት አይቻላቸውም፡፡ ገብተውም እንኳን ቢኾን ድንገት ከእነሱ ቀድሞ የገባ ሰው በመፈወስ ስለሚቀድማቸው ሳይፈወሱ ይመለሳሉ፡፡ ስለዚህም ከውኃው መልሶ የሚያወጣቸውም ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚያወጣቸው አጥተው ሊቸገሩም ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በእንደዚህ ዓይነት ችግር ለባሰ ነገር የተዳረገ በሽተኛም ሊኖር ይችላል፡፡ ከእነርሱ ቀድሞ የሚድነው እንግዲህ ሁለት ዓይነት ሰው ነው፤ አንደኛው በሽታው ለመንቀሳቀስ የማያግደው ኾኖ እያለ የእነሱ ይብሳል ብሎ ሳያዝን የሚገባ ነው፡፡

እንኳን ቀድሞ የገባ ሰው ብቻ በሚድንበት ሥፍራ ቀርቶ በማንኛውም ሰዓት ቢገባ በሚዳንበት የጠበል ሥፍራ ‹‹ከእኔ በሽታ የእገሌ ይብሳል፤ እስኪ ቅድሚያ ልስጠው›› የሚል ሰው ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ደካሞች ቀድመው የሚገቡ በሽተኞች ብዙ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ መጠመቂያው ሊያስገቡት የሚጠባበቁ ዘመዶች ያሉት፣ አለዚያም ዘመድ የሚያፈራበት ገንዘብ ያለው በሽተኛ ደግሞ ሌላው ቀድሞ ወደ መጠመቂያው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የተኛ በሽተኛ (በግእዙ መጻጕዕ) ነበር፡፡ እንግዲህ ሠላሳ ስምንት ዓመት ማለት የጕልምስና ዕድሜ ነው፡፡

መጻጕዕ የመጣው በዐሥር ዓመቱ ነው እንኳን ብንል ዐርባ ስምንት ዓመት ይኾነዋል፡፡ ይህ ሰው ከመታመሙ በፊት ለዚህ ጽኑ ደዌ የሚዳርግ ኃጢአት ለመሥራት የሚችልበት ዕድሜ ላይ መድረሱን ጌታችን ከፈወሰው በኋላ ‹‹ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ›› ብሎ በማስጠንቀቁ እንረዳለን፡፡ መቼም ክፉ ደግ በማያውቅበት ሕፃንነቱ በድሎ ‹‹የልጅነቱ መተላለፍ ታስቦበት ታመመ›› ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ ብቻ ይህ ሰው የአንድ ጐልማሳ ዕድሜ ያህል በአልጋ ላይ ኾኖ በቤተ ሳይዳ ተኝቶአል፡፡ ጠበል ሊጠመቅ ሲጠባበቅ በፀጕሩ ሽበት፣ በግንባሩ ምልክት አውጥቶአል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ግርግም ውስጥ ሲወለድም ይህ በሽተኛ በዚሁ መጠመቂያ ሥፍራ ነበረ፡፡

ድንግል ማርያም የወለደችውን ሕፃን በበረት ውስጥ ስታስተኛው ይህ በሽተኛ አልጋው ላይ ከተኛ ስድስት ዓመት ደፍኖ ነበር፡፡ ከዅሉ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሰው አልጋው ላይ ኾኖ እጅግ ብዙ ሰዎች ቀድመውት ሲፈወሱ ሲመለከት መኖሩ ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ መጥተው ከእሱ በፊት ድነው የሚሔዱ ሰዎችን ማየት እንዴት ይከብደው ይኾን? እንደ እርሱ ብዙ ዘመን የቆዩት ሲድኑ ሲያይ ተስፋው ሊለመልም ይችላል፡፡ በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመደ ብዙ በመኾናቸው ብቻ የሚድኑ ሰዎችን ሲያይ ግን ልቡ በሐዘን ይሰበራል፡፡ ዓመቱ በረዘመ ቍጥር ተስፋ ቈርጦ ቤተ ሳይዳን ቤቴ ብሎ ከመኖር በስተቀር ምንም የሚታየው ነገር አይኖርም፡፡

እግዚአብሔርን በመከራው ውስጥ ተስፋ እያደረገ ይጽናናል እንዳንል ደግሞ እንደ ጻድቁ ኢዮብ ወይም እንደ በሽተኛው አልዓዛር ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ እንደዚያ ቢኾን ኖሮ መቼ ለዚህ በሽታ የሚዳርገው ኃጢአት ይሠራ ነበር? በቃለ እግዚአብሔር ይጽናናል ማለትም ያስቸግራል፡፡ ያም ኾነ ይህ መጻጕዕ በበሽታው እጅግ ተሰቃይቶ ነበር፡፡ ጌታችን የዚህን ሰው ችግር ብቻ ሳይኾን ብዙ ዘመን እንደዚህ እንደነበረ ያወቀው ማንም ሳይነግረው ነበር፡፡ በሽታውን ከነመንሥኤው አስቀድሞ ያውቃልና ወደዚህ የብዙ ዓመታት በሽተኛ መጣና ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› አለው፡፡ ጌታችን የሚፈልገው ይህንን ሰው መፈወስ እንጂ የራሱን ማንነት ማሳየት ስላልነበረ ‹‹ላድንህ ትወዳለህን?›› አላለውም፡፡ በዚያውም ላይ ይህ ሰው የጌታን ማንነት አያውቅም፡፡

ይህ በሽተኛ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ሲባል የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሽታ አመል ያጠፋል፡፡ በሽታው በቆየ ቍጥር ደግሞ መራር ያደርጋል፡፡ ሰዎች በበሽታ ሲፈተኑ በሰው በፈጣሪም ላይ ብዙ የምሬት ንግግር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ጌታችን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ሲጠይቀው ምንም የምሬት እና የቍጣ ቃል ሳይናገር በጨዋ ሰው ሥርዓት ‹‹ጌታ ሆይ …›› ብሎ ነው የመለሰለት፡፡ በዚህ ኹኔታው መጻጕዕ ትሑት ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን የመለሰው የተጠየቀውን አልነበረም፡፡ ጥያቄው ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› የሚል ከኾነ ምላሹ ‹‹አዎን፤ መዳን እወዳለሁ፤›› አለዚያም ‹‹አይ መዳን አልፈልግም›› የሚል ብቻ መኾን ነበረበት፤ እርሱ ግን ‹‹ጌታ ሆይ! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፡፡ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡

መጻጕዕ የጌታችንን ማንነት ባይረዳውም ጌታችን በወቅቱ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበርና ምናልባት ወደ መጠመቂያው ሊጨምረኝ አስቦ ይኾናል ያም ባይኾን ግን ከተከተሉት ሰዎች አንዱን አደራ ሊልልኝ ይኾናል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ‹‹ሰው የለኝም›› ብሎ የሠላሳ ስምንት ዓመታት ብሶቱን ተናገረ፡፡ ‹‹ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› ብሎ እየቀደሙት ሲፈወሱ የነበሩ ሰዎችን አስታወሰ፡፡ ጌታችንም ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ ባላሰበው፣ ባልጠበቀው መንገድ ፈወሰው፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ሲጠባበቃት የነበረችውን የቤተ ሳይዳ ጠበል ሳያገኝ፣ በመልአኩ መውረድ ሳይኾን በመላእክት ፈጣሪ ቃል ተፈወሰ፡፡

ገባሬ መላእክት ክርስቶስ ራሱ መጥቶ አዳነው፡፡ ይህ ሰው ‹‹ለመዳን የሚያስፈልገው ምንድን ነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ የሚመልሰው ‹‹ወደ ውኃው የሚጨምር ሰው እና የቤተ ሳይዳ ውኃ›› ብሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በዚህች ጠበል ካልኾነ በቀር በሌላ በምንም መንገድ ያድናል ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም ነበር፡፡ ጌታችን መጻጕዕ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ተስፋ ያደረጋትን ጠበል ወይም ደግሞ ወደ ጠበሉ የሚጨምሩትን ሰዎች ሳይጠቀም አምላካችን ፈወሰው፡፡ እግዚአብሔር ያለ ጠበልም እንደሚያድን ማመን ካልቻልን እምነታችን ሙሉ አይደለም፡፡

ይህ ሰው ወደ ውኃው ገብቶ ቢድን ኖሮ ‹‹ጌታዬ አዳነኝ›› ከማለት ይልቅ ‹‹መዳን ይነሰኝ? ሠላሳ ስምንት ዓመት እኮ ነው የጠበቅኩት …›› እያለ ልፋቱን ያወራርድ ነበር እንጂ ፈጣሪውን አያመሰግንም ነበር፡፡ ጌታችንም ‹‹ስታምኑብኝ ብቻ ነው የምፈውሳችሁ›› የሚል አምላክ አይደለም፣ ለዅሉም ፀሐይን የሚያወጣ፣ ዝናምን የሚያዘንም አምላክ ይህንን ሰውም ለመፈወስ እስኪያምነው አልጠበቀም፡፡ ጌታችን ጠበል ቦታ ያገኘውን ያለ ጠበል ፈወሰው ሲባል መቼም ጠበል መጠመቅ የማይወዱ ወይም በጠበል የማያምኑ ሰዎች ደስ ሊላቸው ይችላል፡፡

‹‹እኛስ ምን አልን? ጌታ እኮ ይህን በሽተኛ ጠበል ቦታ አግኝቶ እንኳን የፈወሰው ያለ ጠበል ነው›› ብለው ባቀበልናቸው በትር ሊመቱን ይፈልጉ ይኾናል፡፡ ኾኖም በዮሐንስ ወንጌል በዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ዕውር ኾኖ የተወለደውን ሰው ጠበል በሌለበት ሥፍራ አግኝቶት እኛ እመት (እምነት) የምንለውን አፈር በምራቁ ለውሶ ከቀባው በኋላ ‹‹ሒድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ›› ብሎ ልኮታል፡፡ ጠበል ምንም የማያስፈልግ ቢኾን ኖሮ ዓይነ ስውሩን ሰው ወደ ወንዝ ወርደህ ተጠመቅ ብሎ አይልከውም ነበር፡፡ ዛሬ ለታመሙ ሰዎች ‹‹ጠበል ሒዱ›› ብለን ስንመክር ክርስትና ያልገባን፣ ክርስቶስን የማናውቅ የሚመስለው ይኖራል፡፡

አሁን ባየነው ታሪክ ውስጥ ግን ለበሽተኛው ‹‹ሔደህ ጠበል ተጠመቅ›› ብሎ የመከረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መፈወስ የሚቻለው ክርስቶስ ‹‹ጠበል ተጠመቅ›› ብሎ ከተናገረ፤ የታመመን መፈወስ የማንችለው እኛ ኃጢአተኞቹ ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ‹‹ሔደህ ተጠመቅ›› ብንል ምን አጥፍተናል? ጌታችን ሲያደርግ ያየነውን ነው፡፡ ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሎን የለ እንዴ? (ዮሐ. ፱፥፯)፡፡ በእነዚህ ሁለት ታሪኮች አምላካችን ሲፈልግ በጠበል፣ ሲፈልግ ያለ ጠበል፣ አልያም በሕክምና፤ ሲያሻው በምክንያት ሲያሻው ያለ ምክንያት፤ ሲፈልግ በቃሉ፣ ሲፈልግ በዝምታ፤ ሲፈልግ በቅዱሳን መላእክቱ፣ ሲፈልግ ያለ ቅዱሳን መላእክቱ ማዳን እንደሚቻለው እንረዳለን፡፡

ይቆየን