ለማስተጓጎል ተሞክሮ የነበረው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እትም ስርጭት ላይ ዋለ።

ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ለማተሚያ ድርጅቶች በተፃፈ አግባብነት የሌለውና መዋቅሩን ያልጠበቀ ደብዳቤ ለማስተጓጎል ተሞክሮ የነበረው የስምዐ ጽድቅ 18ኛ ዓመት ቁጥር 18 እትም ታትሞ መውጣቱ ተገለጸ። ህትመቱም ስርጭት ላይ ነው።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሣሙኤል ለማተሚያ ቤቶች በፃፉት ደብዳቤ “የማኅበሩ መጽሔት ጋዜጣ በእናንተ በኩል ኅትመት ላይ እንዳይውሉ” በማለት ጠይቀው ነበር።

የማደራጃ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በበኩላቸው ይህ የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ ደብዳቤ ህጋዊ እንዳልሆነ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል። ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለማተሚያ ቤቶች የተፃፈውን አግባብነት የሌለው ደብዳቤ ለማንሣት ይጽፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ማኅበሩ ያሉትን ሚዲያዎች በተመለከተ ከሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አካላት ጋር ለመስራት ምክክር ከጀመረ ቆይቷል ሲሉ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለአማርኛ መካነ ድር ገልጸዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ አጣሪ ኮሚቴ ሠይሞ የማኅበረ ቅዱሳንንና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያን ጉዳይ ለማየት በወሰነበት ውቅት ይሄንን ደብዳቤ መጻፋቸው እንዲህም ለተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫ መስጠታቸው ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል።