ለመነኮሳትና አብነት ተማሪዎች የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐግብር ተዘጋጀ።

በፈትለወርቅ ደስታ
«ሁለት ልብሶች ያሉት….» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ልዩ የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተዘጋጀ
 
የዚህ መርሃ ግብር አዘጋጅ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሲሆን ጥር 22/2003 ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት በይፋ ይከፈታል፡፡ የቅዱሳን መካናት ልማትና ማህበራዊ ዋና ክፍል የቅስቀሳ አስተባባሪ ዲያቆን ደረጀ ግርማ ለማኅበረ ቅዱሳን የሬድዮ ክፍል እንደገለፁት «የመርሃ ግብሩ ዓላማ ብዙዎቹ ገዳማውያን መነኮሳትና የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚለብሱትን እራፊ ጨርቅ ምግባቸውን ያሰጡበታል፤ ያንኑ ምግብ ምግብ እየሸተተ መልሰው ይለብሱና ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡ ይሄንን ማስቀረት ይኖርብናል፡፡ ሌላው ጌታችን መድኃኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 25 ላይ እንደገለጸው፥ «ታርዤ አላለበሳችሁኝም» ከሚለው ወቀሳ ለመዳንና «ታርዤ አልብሳችሁኛልና» የሚለውን ትእዛዝም ለመፈጸም ነው፡፡ በተጨማሪም በአገራችን በአልባሳት የመደጋገፍ ባሕል የለም። ይህ ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ቢያንስ በየሁለት ዓመት አንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት መርሃ ግብር ያስፈልጋል» በማለት ገልጸዋል፡፡

አክለውም «ይህ መርሃ ግብር ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል የአልባሳት ችግራቸው እንዲቀረፍ በ25 ገዳማትና አድባራት ያሉ 75ዐ መነኮሳትና በ5ዐ ታላላቅ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 35ዐዐ መምህራንና ተማሪዎችን በጊዜያዊነት የሚያግዝ ይሆናል፡፡»

በጊዜው የሚሰበሰቡ የአልባሳት አይነቶች ለአብነት ትምህርት ቤቶች ሸሚዝ፣ ሱሪ፣ ኮት፣ ጃኬት፣ ጫማ፣ አንሶላ፣ ጋቢ፣ ብርድልብሶች ካኔተራና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን ለመነኮሳት ደግሞ አቡጀዲ፣ ልብስ፣ ሹራብ፣ ነጠላ እና ለመነኮሳት የሚሆን ሻርፕ፣ ብትን ጨርቅ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

በዝግጅቱ ላይም ከ5ዐዐዐ በላይ ምዕመናን እንደሚሳተፉበት ይገመታል ያሉት አስተባባሪው የአልባሳት ድጋፍ ማድረግ ያልቻሉ ምዕመናን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

«እርስዎ የለበሱት ሌላውን ያለብሳልና» ሁሉም ምዕመን ከዚህ መርሐግብር ለመሳተፍ ወደኋላ እንዳይል አዘጋጅ ክፍሉ ያሳስባል፡፡

የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሃግብር የማኅበረ ቅዱሳንን ሕንፃ ጨምሮ በ15 የሰንበት ትምህርት ቤቶች ይከናወናል፡፡