hosaena

ሆሣዕና(ለሕፃናት)

ሚያዚያ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

hosaenaበኢየሩሳሌም ሀገር ውስጥ በምትገኝ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ከተወለድኩ ዛሬ 5 ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ቀኑ ሰንበት ነው እቤት ውስጥ እየተጫወትኩ እናቴም በጓዳ ሥራ እየሠራች ድንገት የብዙ ሰዎች የእልልታ ድምጽ ሰፈሩ ውስጥ ተሰማ፡፡ እናቴም በፍጥነት ከጓዳ ሮጣ ወጥታ “ልጄ ልጄ ነይ እንሂድ ብላ በጀርባዋ ላይ አዝላኝ ሮጣ ከቤት ወጣች፡፡ እኔም በሁኔታው ተገርሜያለሁ፡፡

በሰፈር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ሁሉ በእናታቸው ጀርባና በአባታቸው ትከሻ ላይ ሆነው ደስ ብሏቸው እንደ ወላጆቻቸው እልል ይላሉ፡፡ ወላጆቻችን ሁሉ ተሰብስበው ከሰፈራችን መውጫ ጋር ወዳለ ትልቅ የዘንባባ ዛፍ ተያይዘው አመሩ፡፡ ከዚያም የዘንባባ ዝንጣፊውን እየቆረጡ ሁሉም ያዙ ለእኛም ሰጡን፡፡ ከዚያ እልል እያልን በደስታ ወደ ቤተ መቅደስ እሮጥን፡፡
በመንገድ ላይ በጣም ብዙ ሕዝብ አየሁኝ ሁሉም ደስ ብሏቸው እነርሱም እንደኛ ወደ ቤተ መቅደስ ይሮጣሉ፡፡ የሕፃናቶቹን ብዛት ሳይ ውስጤ በጣም ደስ አለው፡፡ የገረመኝ ደግሞ የሚያለቅስ ልጅ አንድ እንኳን የለም፡፡ “ዛሬ የኛ የደስታና የዝማሬ ቀን ነው” ማለት ነው ብሎ ልቤ በደስታ ፈነደቀ፡፡

ወደ ቤተ መቅደስ ለመድረስ ጥቂት መንገድ ሲቀረን በርቀት ወደ ቤተ መቅደሱ የሚጓዙ በጣም በጣም ብዙ ሕዝብ ተመለከትኩኝ፡፡ እንደኛ እነርሱም ዘንባባ ይዘዋል፡፡ በመካከላቸው አንድ ትልቅ አህያ አየሁኝ፣ ከአህያይቱም ጋር ልጇ ውርንጫዋ አለች፡፡ የሚያማምር ልብስ በአህያዎቹ ጀርባ ላይ ተነጥፏል፡፡ በውርንጫዋም ላይ የሁላችን ፈጣሪ፣ ንጉሣችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ስመለከት በደስታ ዘለልኩኝ፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆን በጣም ያስደስታል፡፡

ምክንያቱም እኛ ሕፃናትን ሲያይ ደስ ይለዋል፡፡ እቅፍ አድርጎ ስሞን በጉልበቱ ላይ ቁጭ አድርጎን ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡ በዙሪያውም ላሉት ሰዎች እንደነዚህ ሕፃናት ንጹሃን ሁኑ፣ ኀጢአት አትሥሩ፣ እነርሱ አይዋሹም፣ እያለ ይመክራቸዋል፡፡

ከዚያ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ እልል እያለ የሚያመሰግነው ሕዝብና በእናትና በአባቶቻችን እቅፍ ውስጥ ያለነው ሕፃናት በአንድነት ሆነን ጮክ ብለን የዘንባባውን ቅጠል ወደ ቀኝ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ እያውለበለብን መዝሙር መዘመር ጀመርን፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም” የመዝሙሩ ድምጽ በኢየሩሳሌም ከተማ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ደግሞ የእኛ የሕፃናቱ ድምጽ ከትልልቆቹ በልጦ መስማቱ ነው፡፡ ጌታችንን በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ባየሁት ጊዜ ትዝ ያለኝ አባዬ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ያስተማረኝን ታሪክ ልንገራችሁ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ት.ዘካ.9፥9፡፡

የዝማሬውን ድምጽ ሲሰሙ አባታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱት እና የሚያሳድዱት በከተማው ውስጥ ያሉ ጨካኝ ሰዎች እኛ ተሰብስበን እየዘመርን ወደአለንበት መጡ፡፡ ሲመለከቱ ሕዝቡ ሁሉ ደስ ብሏቸው እየዘመሩ እልል እያሉ የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለቡ ኢየሱስ ክርስቶስን በአህያዋ ውርንጫ ላይ አስቀምጠው እያመሰገኑት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ተመልክተው ጨካኞቹ ሰዎች በጣም ተናደው ሕዝቡን “ዝም በሉ” ብለው ተቆጧቸው፡፡ ትልልቆቹ ሁሉ ፈርትው ዝም አሉ፡፡

እኔና ጓደኞቼ ግን በእናታችን ጀርባ ላይ ካሉት ሕፃናት ጋር አብረን ሆነን ጮክ ብለን “ሆሣዕና በአርያም” የሚለውን መዝሙር መዘመር አላቆምንም ነበር፡፡ የገረመኝ ደግሞ ከእኔ የሚያንሱት ገና የተወለዱትም ሕፃናት መዝሙሩን ጮክ ብለው ሲዘምሩት በመስማቴ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ መናገር የማንችለውን እኛን እንድንዘምርልህ ስለፈቀድክልን ተመስገን፡፡” ብዬ አመስግኜ መዝሙሩን መዘመር ቀጠልኩኝ “ሆሣዕና፣ ሆሣዕና፣ ሆሣዕና በአርያም….”

እነዚህ ጨካኞቹ ሰዎች ግን እናትና አባቶቻችንን ዝም አስብሏቸው ብለው ሲያስፈራሩዋቸው ወላጆቻችን ፈርተው የሁላችንንም አፋችንን ይዘው ዝም አስባሉን፡፡ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋ ውርንጫ (በትንሿ አህያ) ላይ ቁጭ ብሎ ለጨካኞቹ ሰዎች እንዲህ አላቸው “ከሕፃናት ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራሴ አዘጋጅቻለሁ፡፡ የእነርሱንም አፍ ይዛችሁ ዝም ብታስብሏቸው በዙሪያዬ ያሉት ድንጋዮች ያመሰግኑኛል፡፡ የፈጠርኳችሁ ድንጋዮች ሆይ ሕፃናት እንደዘመሩ እናንተም በመዝሙር አመስግኑኝ፡፡” በማለት በታላቅ ድምጽ ሲናገር፤ ትልልቁም ድንጋይ፣ ትንንሹም ድንጋይ ከመሬት ወደ ላይ እየተነሡ “ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቀርባለን ምስጋና…” እያሉ በጣም ደስ በሚል ድምጽ መዘመር ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ ጨካኞቹ ሰዎች አፍረውና ፈርትው ሄዱ፡፡

እኛም ወላጆቻችንም በዙሪያችንም ያሉትም ድንጋዮች አምላካችንን ከበን በእልልታ እየዘመርን ለአህያዎቹ መርገጫ ልብሳችንንና የዘንባባውን ዝንጣፊ እያነጠፍን ወደ ቤተ መቅደስ ገባን፡፡ በዚያም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚል ትምህርት አስተማረን፡፡

በመጨረሻም ሆሣዕና ብለን ምስጋና ላቀረብነውና በቤተ መቅደስ ተገኝተን ቃሉን ለምንሰማው ሕፃናት እንዲህ ብሎ መከረን “ልጆቼ በመዝሙራችሁ ተደስቻለሁ፣ ሁል ጊዜ ወደ ቤቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኑና ዘምሩልኝ፡፡ አፋችሁ በመዝሙር ይዘምር እንጂ ዘፈን እንዳይዘፍን አደራችሁን፡፡ ዘፈን መዝፈን ኀጢአት ነው፡፡”

ትምህርቱን ጨርሰን ከእናቴ ጋር ደስ እያለን ወደ ቤት ተመለስን፡፡ ታዲያ ሁል ጊዜ ይህችን የሆሣዕናን በዓል በውስጤ አስባታለሁ፣ መዝሙሩን መዘመር በጣም ያስደስተኛል፡፡ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የመከረኝንም ምክር ጠብቄ ዘፈን የሚባል በአፌ ሳልዘፍን መዝሙር እየዘመርኩኝ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩኝ አደኩኝ፡፡

ልጆችዬ ዛሬ የምታነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚሆነው ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 እስከ ቁጥር 16 እና ማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 17 ያለውን ይሆናል፡፡ ሆሣዕና በአርያም ብለን እንድናመሰግነው ኀይሉን የሰጠን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡፡