ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ካለፈው የቀጠለ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቀሲስ ስንታየሁ አባተ አባባል የፍልሰታ ጾም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ይህም ከእመቤታችን ጋር ያለንን የጠበቀ ትስስር የሚያመላክት ሲኾን ከዚህም ሌላ አገራችን ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር ናት፡፡ እመቤታችን ልጇ ወዳጇ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ይዛ በተሰደደችበት ወቅት በግብጽ ብቻ ሳይኾን በኢትዮጵያ ምድርም መጥታ ዐርፋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አራቱንም የአገሪቱን መዓዝን ባርካለች፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩት ነቢዩ ዕንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ›› በማለት የተናገረው ትንቢትም እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሥርዓት አድርገን ፍልሰታን በልዩ ኹኔታ እንጾማለን፡፡

ድርሳነ ዑራኤልም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ወራት ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ከምድረ እስራኤል ወደ ምድረ ግብጽ፣ ከዚያም ወደ ብሔረ ኢትዮጵያ መጥታ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት በደብረ ዳሞበትግራይ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በደብር ዐባይ፣ በጐጃምና በጣና በአደረገችው የስደት ጉዞ ሕፃኑ ኢየሱስ ለድንግል እናቱኢትዮጵያን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ››› በማለት በሸዋና በወሎ፣ በሐረርጌና በአርሲ፣ በሲዳማና በባሌ፣ በከፋና በኢሉባቦር፣ በወለጋና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍላተ አህጉር በብሩህ ደመና ተጭነው በአየር እየተዘዋወሩ ተራራውንና ወንዙን (አፍላጋቱን) እንደ ጐበኙ ይናገራል፡፡ ይህም የቀሲስ ስንታየሁን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት የምእመናን ቅድመ ዝግጅት

በጾመ ፍልሰታ ወቅት ምእመናን ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው? ሱባዔ ከገቡ በኋላስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? የሚለውም ሌላው ጥያቄአችን ነበር፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እንዲህ ይመልሳሉ፤

‹‹ምእመናን ጾም (ሱባዔ) ከመጀመራቸው በፊት የሥጋን ኮተት ዅሉ ማስወገድ አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ዅሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባዔ የሚያቋርጣቸውን ጉዳይም አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡ በኋላሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ተሰጣቸው ጸጋ መጠን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመን መርዳት የማይችል ደግሞ ምክርና ሐሳብ በመስጠት ክርስቲያናዊ ድርሻውን ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂት በመመገብ፣ ብዙ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን ያህል እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተም ሥርዓት ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ  ልብስ መኾን የለበትም፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ የተናገሩትም ከሊቀ ማእምራን ደጉ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እንዲህ ይላሉ ቀሲስ፤ ‹‹ጾም ማለት ለእግዚአብሔር ማመልከቻ ማስገባት ማለት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ሦስት ቀን ጾሙ፤ በሦስት ቀናት ውስጥ አገራቸው ከመከራ ዳነች፡፡ የፍልሰታ ጾምም የወገኖቻችንን፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ጥፋት አታሳየን› ብለን ቦታና ጊዜ ወስነን ሱባዔ የምንይዝበት ጾም ነው፡፡ እኛ ምእመናን ከሁለት መቶ ኀምሳ ቀናት በላይ እንጾማለን፡፡ ነገር ግን ስንጾም ማየት የሚገባን ነገር አለ፡፡ ፍቅር እንደ ሸማ ያላብስህ እንደሚባለው ስንጾም ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾም ያለ ፍቅር፣ ፍቅርም ያለ ጾም ዋጋ የለውም፡፡ ቁም ነገሩ እኛ በጾም ደርቆ መዋል ሳይኾን ፍቅርና ሰላም መታከል አለበት፡፡ የተጣላ መታረቅ አለበት፡፡ በቅዳሴ ሰዓት ቦታ ላጡ ቦታ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ በተለይ አረጋውያንንና ሕፃናትን መደገፍ የወጣቶች ድርሻ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የበረታው ለደከመው ቦታ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሐሜትናሁካታቂም በቀል ያዘለ ንግግር ቦታ ሊኖረው አይገባም፡፡››

እንደ ቀሲስ ስንታየሁ ገለጻ ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ከኾነ ለምንድን ነው በጾማችን፣ በጸሎታችን ኅብረተሰባችን ከጉስቁልና ያልወጣው? ብለን ብንጠይቅ ሳይጾም ሳይጸለይ ቀርቶ ሳይኾን ፍቅር ስለሌለው ነው እንጂ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፊትም አሁንም ኾነ ወደፊት የሕዝቡን ልመና ይሰማል፡፡

ሱባዔ የገቡ ዅሉ ራእይ ያያሉን?

ለሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እና ለቀሲስ ስንታየሁ አባተ በመጨረሻ ያነሣንላቸው ጥያቄ ራእይ ከማየትና አለማየት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲታመሙ ከሕመማቸው ለመፈወስ ወይም በምድራዊ ሕይወት ለሚያነሧቸው ጥያቄዎች መፍትሔ ለማግኘት ሱባዔ በመግባት ራእይ ማየት አለብን ይላሉ፡፡ ራእይ ካላዩ ደግሞ ተስፋ ይቈርጣሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የምታስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መምህራኑ ምላሽ አላቸው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ፡- ‹‹ምንም እንኳን ወሩ ከሌላው በተለየ የሱባዔና የራእይ ወቅት ኾኖ ቢገለጽም በፍልሰታ ጾም ራእይ ማየት አለማየት የሚለው የብቃት መለኪያ (ማረጋገጫ) መኾን የለበትም፡፡ ቦታ ቀይረውና ከሰው ተለይተው እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት መጠየቅ በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዟል፡፡ ምእመናን ወደ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንወቅ ብለው እርሱን ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሳካላቸው በተለያየ ጊዜ በሱባዔው ይቀጥላሉ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም›› ሲሉ ምእመናንን መክረዋል፡፡

ቀሲስ ስንታየሁም፡- ‹‹አንድ ሰው የሚጾመው ራእይ ልይ ብሎ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን ሲጾሙ፣ ሲጸልዩ ኃጢአታቸው እንዲገለጽላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው አይደለም፡፡ ኃጢአታን ከተገለጸልንና ንስሐ ከገባን እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ተሞልቶ እግዚአብሔርን ልይ ቢል ሊኾን አይችልም፡፡ እኛንና እግዚአብሔርን የሚለያየን ኃጢአትና በደል ነው፡፡ ስለዚህ የሚያራርቀንን ነገር ለማስወገድ መጾም አለብን፡፡ ምእመናን በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ችግር፣ ለሰው ልጅና ለአገር የሚበጅ ነገር አምጣልን ብለው ሱባዔ በመያዝ መጾም መጸለይ ይገባቸዋል እንጂ ራእይ እንዲገለጥላቸው መጓጓት፣ ራእይ አላየንም ብለውም ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም፤›› በማለት መንፈሳዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያህል በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት፤ እንደዚሁም መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ምእመናን በምንጾምበት ወቅት የተራቡትንና የታረዙትን በማሰብ ካለን ከፍለን ለተራቡና ለታረዙ ማብላት፣ ማልበስ ይገባል፡፡ ይህን የምናደርገውም በፍልሰታ ወይም በሌሎችም አጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይኾን በማንኛውም ጊዜ ነው፡፡ የተቸገሩትን መርዳት ወይም እርስበርስ መረዳዳት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግዴታ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባህልም ነውና፡፡ ይህ ጾም ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን የምናሰፍንት፤ መንፈሳዊ ዕድገትን የምናመጣበት ይኾንልን ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት አይለየን፡፡

                                                              ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡