የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው? – ክፍል አንድ

በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዐቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት አምስተኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጕሙ ‹‹የወይራ ዛፍ፣ ተራራ›› ማለት ሲኾን፣ ይህም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?›› /ማቴ.፳፬፥፫/ ብለው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጠየቁት ጊዜ እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶች ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ለምእመናኑ ታስተምራለች፡፡ በመኾኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን የሚመለከቱ ምሥጢራት በሰፊው ይነገራሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት በዓለም እየተከሠቱ ያሉ ወቅታዊ ምልክቶችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ጋር በማገናዘብ መጠነኛ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤

የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከእነዚህም በተለይ በደብረ ዘይት ዕለት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?›› በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋነኛውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲሕ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጕሙ ‹‹ሐሰተኛ የኾነበኢየሱስ ክርስቶስ (በአምላክ) ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ›› ማለት ነው፡፡

ትርጕሙን አስፍተን ስንመለከተው ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥነት ያላቸውም ኾነ የሌላቸው፣ በዓለም ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች በማወቅም ይኹን ባለማወቅ በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት፣ የሥነ ተፈጥሮ፣ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንደዚሁም ሰብአዊ ክብር፣ መንፈሳዊና አገራዊ ባህል አገራዊ እንዲጠፋ የሚሠሩ አካላት ዅሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክት አንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ ጉዳዩን ለማብራራት ያህል የሚከተሉት ነጥቦችን እንመልከት፤

፩. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ

እግዚአብሔር በመጻሕፍቱ ‹‹አባቶችህ ያኖሩትን (የሠሩትን) የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፋልስ›› /ምሳ.፳፪፥፳፰/ በማለት ያዘዘውን ትምህርት መጣስ ማለትም የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ ከሐሳዊ መሲሕ ተግባር ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ አፈጻጸሙም ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ኹኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ‹‹‹እኔ ክርስቶስ ነኝ› እያሉ ብዙ ሰዎች በእኔ ስም ይነሣሉ›› /ማቴ. ፳፬፥፭/፡፡

ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ እንደ ኾነ የማይሰብክ ዅሉ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ዅሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ፤›› በማለት በእነዚህ ሐሳውያን ላይ ይመሰክርባቸዋል /፩ኛዮሐ. ፬፥፫/፡፡

በመኾኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው እንደ ተነሡት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ፭፥፴፮-፴፯/፤ ከዚያም በኋላ በየጊዜው እንደ ተነሡ መናፍቃን በዚህ ዘመንም ‹‹ኢየሱስ ነኝ … ኢየሱስ በእኛ ዘንድ አለ …›› እያሉ የዋሁን ሕዝብ የሚያጭበረብሩ ሐሳውያን መሲሖች መጥተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ (ሎቱ ስብሐት)፣ ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት (ቁሳዊነት) ወይም በኢቮሉሽን (በዝግመተ ለውጥ) ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ፣ ወዘተ. ዅሉ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡

አሁንም ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ልጆች ሆይ! መጨረሻው ሰዓት ነው፤ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፡፡ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ እናውቃለን፤›› ይለናል /፩ኛዮሐ. ፪፥፲፰/፡፡ ከዚህ ቃል የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መኾኑን ነው፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ ከሚያመለክቱ፣ ከሐሳዊው መሲሕ እና ከእርሱ ጋር ተዛማጅ የኾኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን ለመረዳት የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣

‹‹የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ዅሉ ሊያስገድላቸው፣ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለ ጠጋዎችና ድሆችም፣ ጌታዎችና ባሪያዎችም ዅሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፡፡ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፤›› /ራእ. ፲፫፥፲፮-፲፰/፡፡

ይህ የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ከሚመሠጠርበት ትርጕም ውስጥ አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ‹‹የሚናገር የአውሬው ምስል›› ማለት ለእርሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ‹‹ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል›› ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሠለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ በዘመናዊ (ኮምፒውተራይዝድ) መንገድ የተደራጀ በመኾኑ፣ ከዚህ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር ማንም ሰው በዚያች አገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ. አይችልም፡፡ በዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ አንድ ሰው ወደየትኛውም ዓለም ቢንቀሳቀስ በጣቱ አሻራ ይታወቃል፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በትንቢቱ፡- ‹‹አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፤ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፤››  የሚለውም ይህን ጉዳይ የሚያደራጀው ሌላ አካል ሳይኾን የሰው ልጅ መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ‹‹ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት›› የሚለው ቍጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡

ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስለው የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ በአጠቃላይ ቅዱሳንን መስደብ ነው፡፡ እነዚህ በልዩ ልዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ተግባራት ዛሬም ተጠናክረው በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶአውያን መናፍቃን ትልቁ ሤራ የእግዚአብሔር ወልድን አምላክነት፤ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፤ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፤ የቅዱሳንን ቅድስና እና አማላጅነት መቃወም ነው፡፡ የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መኾኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፤

‹‹ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፡፡ ለአውሬውም ‹አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?› እያሉ ሰገዱለ፡፡ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፡፡ በዐርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ዅሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ዅሉ ይሰግዱለታል፤›› /ራእ. ፲፫፥፬-፰/፡፡

ሌላኛው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብርን፣ ዝናንና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቍጠር ከሐሳዊው መሲሕ ጋር ያስመድባል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደ ገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናስተውል የተነሡበት ዋነኛው ነጥብ ‹‹ስማችንን እናስጠራ›› የሚለው ነበር፡፡ ‹‹‹ኑ! ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው› አሉ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘፍ. ፲፩፥፬/፡፡ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት ነው እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትና የተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራና ሥራቸውን ሲያደንቅ እንዲኖርላቸው ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

፪. የሥነ ተፈጥሮ ሕግመጣስ

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመኾኑ ይህ ቀረህ፤ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ሰው ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ለማግኘት ሲል ዝርያቸው የተለያየ ፍጥረታትን (እንስሳትና ተክሎችን) ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቍጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ የሰውን ቍጥር ለመቀነስ በሚደረጉ ሕክምናዎች ምክንያትም ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዚህ መሰሉ ድጋፍና ማበረታቻ በተለይ በሠለጠኑ የዓለም ክፍሎች ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ኾነዋል፡፡

ይህም አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣልና በመጣስ ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ መኾኑንና የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡ ለዚህም ነው ሊቀ ነቢያት ሙሴን፡- ‹‹ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤›› ሲል ያዘዘው /ዘሌ. ፲፱፥፲፱/፡፡ ግብረ ሰዶምን በተመለከተም ‹‹ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፡፡ ደማቸው በላያቸው ነው፤›› ተብሎ ተጽፏል /ዘሌ. ፳፥፲፫/፡፡

፫.  ጋብቻን ማፍረስ (ማፋታት)

አውሬው (አስማንድዮስ የሚባለው ርኵስ መንፈስ) የጋብቻ ጠላት ኾኖ ነግሦአል፡፡ ስለዚህም ተጋቢዎች ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና በአንድ መኖራቸውን ጠልተው ይለያያሉ (ይፋታሉ)፡፡ አስማንድዮስ (ርኵስ መንፈስ) ከጋቻ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው ወንድን ከወንድ፣ ሴትን ከሴት ጋር እያቆራኘ በማምለኪያ ሥፍራዎቻቸው ሳይቀር ጋብቻቸውን እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ይህንን ኀጢአት በሚመለከትም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤

‹‹ስለዚህ እርስበርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፡፡ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፡፡ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፡፡ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ዓመፃ ዅሉ፣ ግፍ፣ መመኘት፣ ክፋት ሞላባቸው፡፡ ቅናትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ክርክርን፣ ተንኰልን፣ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፡፡ የሚያሾከሹኩ፣ ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ የሚያንገላቱ፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክህተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ምሕረት ያጡ ናቸው፡፡ ‹እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል› የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም፤›› /ሮሜ.፩፥፳፬ እስከ ፍጻሜው/፡፡

 ይቆየን