‹‹የአሁኑ እሳት በቍጥጥር ሥር ቢውልም ለወደፊቱ ግን ያሠጋናል … ልጁ ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡›› የገዳሙ አበምኔት

ze1

ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አካባቢ (ዙርያ) መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቀትር ላይ ተነሥቶ የነበረው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ በቍጥጥር ሥር መዋሉን የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሕይወት አስታወቁ፡፡

ከገዳሙ አባቶች አንዱ አባ ጥላኹን ስዩም እንዳብራሩት እሳቱ የተነሣበት አካባቢ ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ከመኾኑ ባለፈ ቃጠሎው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቈጣጠር ባይቻል ኖሮ ከደኑም አልፎ ተርፎ በገዳሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር፡፡

zuquala

የዝቋላ ገዳም መገኛና የአካባቢው መልክዐ ምድር

የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የልዩ ልዩ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እሳቱን ለማጥፋት በመረባረብ ክርስቲያናዊ ሓላፊነታቸውን የተወጡ ሲኾን፣ በወቅቱ ከገደል ላይ ወድቆ በመጎዳቱ ሕክምና ሲደረግለት የነበረው ኦርቶክሳዊ ወጣት ሸገና ሉሉ (የክርስትና ስሙ ወልደ ዮሐንስ) ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የአዳማ ማእከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሕይወት ‹‹ልጁ ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡ ከሰማዕታት እንደ አንዱ የሚቈጠር ነው›› ሲሉ የወልደ ዮሐንስ መጠራት ሰማያዊ ዋጋ የሚያስገኝ ሞት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ወቅቱ ሌሊት በመኾኑ፣ በዚያውም ላይ ልጁ የአካባቢውን ተፈጥሮ ባለማወቁ ለኅልፈት ቢዳረግም ሞቱ ግን የሚወደድ እንጂ የሚያስቈጭ አይደለም›› ያሉት ደግሞ አባ ጥላኹን ስዩም ናቸው፡፡ በመጓጓዣ እጦት ምክንያት ማኅበረ መነኮሳቱ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ለመገኘት እንዳልቻሉ ያስታወሱት አበምኔቱ ለወጣቱ በገዳሙ ጸሎተ ፍትሐት እንደተደረገለትና ለወደፊቱም ቤተሰቦቹን ለማጽናናት ኹኔታዎችን እያመቻቹ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

%e1%8b%9d2

የእሳት ቃጠሎውን ለማጥፋት የምእመናን ተሳትፎ

አበምኔቱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት በገዳሙ አባቶች፤ በአካባቢው ነዋሪዎችና ከልዩ ልዩ ቦታዎች በመጡ የቤተ ክርስቲያን የቍርጥ ቀን ልጆች፤ እንደዚሁም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ አየር ኃይል፤ በኦሮምያ ፖሊስ እና በሊበን ወረዳ ፖሊስ ርብርብ ለገዳሙ ሥጋት የነበረው ይህ ከባድ ቃጠሎ በቍጥጥር ሥር ውሏል፡፡ የበረኃውን ሐሩር፣ የእሳቱን ወላፈን፣ እሾኽና ጋሬጣውን፣ ረኃቡንና ጥሙን ተቋቁመው እሳቱን በማጥፋት ገዳሙን ከጥፋት የታደጉ አካላትን ዅሉ አበምኔቱ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም አመስግነዋል፡፡

‹‹ገዳማችን በስም የገነነ ነገር ግን በብዙ ችግርና ፈተና ውስጥ ያለ ገዳም ነው፡፡ የአሁኑ እሳት በቍጥጥር ሥር ቢውልም፤ ለወደፊቱ ግን ያሠጋናል፡፡ በየዓመቱ በየካቲትና መጋቢት ወሮች ‹እሳት መቼ ይነሣ ይኾን?› እያልን እንጨነቃለን፡፡ ችግሩን ለማስቀረትና ጋታችንን ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገናል፤›› ያሉት አበምኔቱ፣ በመጨረሻም ገዳሙ ያለበትን ችግር ለመፍታትና የእሳት ቃጠሎውንም በዘላቂነት ለመቈጣጠር ያመች ዘንድ በገዳሙ የታቀዱ የገቢ ማስገኛ ተግባራትንና በጅምር የቀረውን የውኃ ጕድጓድ ለመፈጸም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ ቢያደርግልን፣ ገዳሙ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን የአገርም ሀብት ነውና መንግሥትም መንገድ ቢሠራልን ሲሉ በቤተ ክርስቲያን ስም የርዳታ ጥሪአቸውን ያቀርባሉ፡፡

ziquala

ቃጠሎው በደኑ ላይ ያደረሰው ጉዳት በከፊል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕፀዋቱን ለማገዶና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙ አካላት በመበራከታቸውና በተደጋጋሚ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በደን የተሸፈነው ግዙፉ የዝቋላ ተራራ በመራቆት ላይ እንደሚገኝ፤ በሰሞኑ ቃጠሎም አብዛኛው የደን ክፍል እንደወደመ ከልዩ ልዩ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምም ቍጥቋጦ በሚበዛበት፣ ነፋስ በሚበረታበት፣ በረኃማና ወጣገባ መልክዐ ምድር ላይ የሚገኝ በመኾኑና በሌላም ልዩ ልዩ ምክንያት በተደጋጋሚ በእሳት ተፈትኗል፡፡ ለአብነትም መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም በገዳሙ ዙርያ ተነሥቶ በነበረው ከባድ ቃጠሎ በደኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡

መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በገዳሙ አካባቢ የተነሣውን እሳት ለማጥፋት ሲሯሯጥ በሞት ለተለየው ወጣት ሸገና ሉሉ (ወልደ ዮሐንስ) ሰማያዊ ዕረፍትን፣ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን እየተመኘን የቤተ ክርስቲያችንንና የአገራችንን ሀብት የዝቋላ ገዳምን ህልውና ለማስጠበቅ፣ ገዳሙ ያለበትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ደኑንም ወደ ነበረበት ተፈጥሮ ለመመለስ ይቻል ዘንድ የሚመለከተን ዅሉ ብናስበበት መልካም ነው እንላለን፡፡