የቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ የቅኔ ጉባኤ ቤት የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት

 

የእሳት ቃጠሎ ደረሰበትየቅኔ ጉባኤ ቤቱ

                                                       ዲ.ን ዘአማኑኤል አንተነህ               

በጎንደር ከተማ የሚገኘው የቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት፡፡ የጉባኤ ቤቱ አለቃ መምህር ናሆም አዝመራው የእሳት ቃጠሎ የተቀሰቀው በኤሌክትሪክ ምክንያት መሆኑን አስረድተው በአደጋው ምክንያት ከ120 በላይ ጎጆዎች መቃጠላቸውንና ፤ ከ30 በላይ ጎጆዎች መፈራረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በቃጠሎው ሳቢያ የተማሪ ጎጆዎች እና ልብሶቻቸው፣የጉባኤ  ቤቱ የማኅበር ቤት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ  ግስ፣ ዝክረ ቃል፣ መዳልው፣ ዳዊት፣ ሰዓታት፣ ሃይማኖተ አበው፣ ስንክሳር፣ አገባብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ታሪክ፣ አንድምታ ወንጌል እና የመሳሰሉት በርካታ መጻሕፍት ተቃጥለዋል፡፡

በአደጋው ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ያለ መጠለያ የቀሩ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ባሠራው ዐሥር የማደሪያ ክፍሎች፣በመቃብር ቤት፣በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰንበቴ ቤት በጊዜያዊነት  የአብነት ተማሪዎቹ  ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

“የተማሪ ቤት መቃጠል የነገይቱን ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መፍለቂያ ጠፋ ማለት መሆኑን ያስረዱት የጉባኤ ቤቱ መምህር ወላዴ አእላፍ ጌዴዎን አበበ “ሁሉም ክርስቲያን የተቃጠለውን የቅኔ ጉባኤ ቤት ወደነበረበት ለመመለስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል”ብለዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ከተማ ከሚገኙ የቅኔ ጉባኤ ቤቶች የቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ የቅኔ ጉባኤ ቤት አንዱ ሲሆን በጉባኤ ቤቱ ከ500 በላይ ተማሪዎች እና ከ20 በላይ አስነጋሪዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሊቃውንቱ መፍለቂያ እንዲህ እንደምታዩት ሆነ

በእሳት የወደመው ጉባኤ ቤቱ