ዝክረ በዓለ ጥምቀት

timk

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

በዓለ ጥምቀት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንደ በዓለ መስቀል በዐደባባይ የምታከብረው ልዩ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር አገራዊ ቅርስም ነው፡፡ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው ደማቅ መንፈስ ከተማዋን ታላላቅ እንግዶችን በቤቷ ለመቀበል ሽር ጉድ የምትል አንዲት ወይዘሮን አስመስሏታል፡፡ በየቦታው በተዘጋጁ ድንኳኖች የሚሰሙ ኦርቶዶክሳውያን መዝሙራት፤ ነጭ ልብስ ለብሰው የሚንቀሳቀሱ ምእመናን፤ በየቤቱ የነበረው ባህላዊ ዝግጅት ልዩና ማራኪ ነበር፡፡ ይህ ልዩ በዓል እንደ አሁን በፊቱ ዅሉ በዘንድሮው ዓመትም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በደማቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሮ ውሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጊዜያዊው የጥምቀት ቤተ መቅደስ በጃንሜዳ የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት በተሰባሰቡበት በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ የተከበረው የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ጥምቀት ከዋይዜማው ጀምሮ መንፈሳዊ ቀልብን በሚገዙ፤ ልቡናን በሚመስጡ፣ ሕሊናን በሚማርኩና ነፍስን በሚያስደስቱ ሥርዓታት ተውቦ ነበር፡፡

በትምህርተ ወንጌል፣ በዝማሬ፣ በዕልልታ፣ በጸሎተ ቅዳሴ፤ በቦታው የተገኙ የቤተ ክርስቲያችን አባቶች (ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምህራን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት)፤ እንደዚሁም የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፤ ከየአጥቢያው ታቦታቱን በዝማሬ አጅበው የመጡ የሰንበት ት/ቤት እና የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን፤ የበዓሉን ሥርዓት ለመመልከት ከውጪ አገር እና ከአገር ውስጥ የመጡ ጐብኚዎች፤ በበዓሉ ለመታደም በነቂስ ከየቤታቸው ወጥተው በጃን ሜዳ የተሰባሰቡ በመቶ ሺሕ የሚቈጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ እና የአካባቢው ምእመናን ጃን ሜዳን ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ፍርድ የሚሰጥበት ዐውደ ምሕረትን አስመስለውታል፡፡

pp

እኛም በጃን ሜዳ ተገኝተን በዓሉን አክብረናል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በዋይዜማው (የከተራ ዕለት) በጃንሜዳ ተገኝው ስለ ጌታችን ጥምቀት ካስተማሩት ቃለ እግዚአብሔር በተጨማሪ በዕለቱም ‹‹ወይርአይ ኵሉ ዘነፍስ አድኅኖቶ ለእግዚአብሔር፤ ነፍስ ዅሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤›› /ሉቃ.፫፥፮/፣ በሚል ኃይለ ቃል በሰጡት ቃለ ምዕዳናቸው የሰውን ልጅ ለሞት ያበቃው ኀጢአት በጥምቀተ ማይ እና በልደተ መንፈስ ቅዱስ መወገዱን ማስተማራቸውም አንዱ የበዓሉ በረከት ነበር፡፡

ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየጎዳናው፣ በየመንደሩ፣ በየወንዙ ቅዱስ የኾነውን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ይዛ በመዝሙር፣ በጭብጨባ፣ በሆታ፣ በዕልልታ፣ በውዳሴ፣ በማኅሌት፣ በቅኔ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በጸሎት የከበረውን ውኀ ባርኮ በመርጨት ልዩና በኾነ የአምልኮ ጉዞ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አስተምህሮን አጉልቶ ሊያሳይ በሚያስችል መልኩ በዓለ ጥምቀት እንዲከበር በማድረጓ ለአገራችን ኢትዮጵያ ልዩ የኾነ ግርማ ሞገስን አጐናጽፋ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡ ከ፶ ሚሊየን በላይ የሚኾን ሕዝበ ክርስቲያን በነጻነት፣ በአንድነት፣ በደስታና በፍቅር ከቤተ ክርስቲያኑ አንሥቶ እስከ ባሕረ ጥምቀቱ፤ ከባሕረ ጥምቀቱ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ ምንም መለያየት ሳይኖር፣ ጥላቻ ሳያጋጥም፣ በየቋንቋውና በየባህሉ ፈጣሪውን እያመሰገነ እንደ ዓባይ ወንዝ የእግዚአብሔር ሠራዊት ኾኖ ከዳር እስከ ዳር እየተመመ በዓለ ጥምቀትን ማክበሩ ዅሉን የሚገዛ የእግዚአብሔር ኀይል መገለጫ መኾኑን ቅዱስ ፓትርያኩ አስገንዝበዋል፡፡

img_0513

‹‹ይህ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወትና የሥራ ፍሬ ምስክር ነው፡፡ ይህ በዓል የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አበው የማይፈርስ ጽኑዕ ግንብ ነው፡፡ ይህ በዓል የኢትዮጵያ እና የእግዚአብሔር የኾነ ጽኑዕ የቃል ኪዳን ትስስርን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው፤›› ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስበርስ ከማቀራረብና ከማስተሳሰር አኳያ ከበዓለ ጥምቀት የሚበልጥ በዓል እንደሌለ ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን ይህንን ጸጋ እግዚአብሔርና ግርማ ሞገስ የተሞላ በዓል እስከ መጨረሻው ሊጠብቁትና ሊንከባከቡት፤ ሊያሳድጉትና ሊያበለጽጉት፤ ለዓለምም ሊያስተዋውቁት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ እና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ እንደዚሁ በበዓለ ጥምቀት ዋይዜማ ከሰጡት ትምህርተ ወንጌል በተጨማሪ በዕለቱም ‹‹ተሣሃልከ እግዚኦ ምድረከ ወሜጥከ ፄዋሁ ለያዕቆብ ወኀደገ ኀጢአቶሙ ለሕዝብከ፤ አቤቱ ምድርህን ይቅርል አልኽ፡፡ የያዕቆብን ምርኮ መለስህ፡፡ የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር አልህ፤›› /መዝ.፹፬፥፩/ በሚል ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላካችን አዳምን ከዘለዓለማዊ ሞት ማዳኑን እና ለሕዝቡ ያደረገውን ይቅርታ የሚያስገነዝብ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

img_0506

በበዓሉ ከታደሙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት መካከል የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ወልደ ማርያም ያስተላለፉት መልእክት ደግሞ ሌላው የጥምቀት ትውስታ ነው፡፡ ሚኒስትሯ በዚህ መንፈሳዊ በዓል ላይ ተገኝተው መልእክት ለማስተላለፍ በመቻላቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸው ኢትዮጵያውያን የብዙ ሀብት ባለቤት የኾነች አገር ስላለችን ዕድለኞች እንደ ኾንን እና አገራችን ካሏት ልዩ ልዩ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብታት መካከል በዓለ መስቀል አንዱ መኾኑን ጠቅሰው ይህንን የማይዳሰስ ሃይማኖታዊ ሀብት ጠብቀው ለትልድ ያቆዩ ቀደምት ኢትዮጵያውያንን አመስግነዋል፡፡ ዶ/ር ኂሩት አያይዘውም ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጐብኚዎች በአንክሮ እና በተደሞ ኾነው የበዓሉን ሥርዓት እንዲከታተሉ ያደረጋቸው በዓለ ጥምቀት በሌላው ዓለም የማይገኝ፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ኾነው ደስታቸውን የሚገልጹበት ልዩ በዓል በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡

በዓለ ጥምቀት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት እንዲመዘገብ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ ለዚህም ቤተ ክርስቲያንና መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አብያተ መዝክራትን በማስፋፋት መንፈሳዊ ቅርሶችን የመጠበቅ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኗ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ኂሩት ወልደ ማርያም በመጨረሻም ‹‹በበዓለ ጥምቀት አከባበር ላይ የሚታየው የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ ኅብረት በማኅበራዊ ሕይወታችንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ›› በማለት መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ አቶ ገብረ ጻድቅ ሀጎስ እንደዚሁ በዓለ ጥምቀት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚገነባ እና ለዓለም የሚያስተዋውቅ በዓል ከመኾኑ ባሻገር ለአገሪቱ የቱሪዝም ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡

img_0514

በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ጥምቀት ወቅት አባቶች ካህናት ከዋይዜማው ጀምሮ ከምግብ ተከልክለው፤ እንቅልፍ አጥተው በቅዳሴ፣ ታቦት በማክበርና በመሳሰሉ ተልእኮዎች መሰማራታቸው፤ የየአድባራቱና ገዳማቱ ሊቃውንት፣ የየሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ፣ በዋሽንት፣ በበገና ታግዘው የሰሚዎችን ልቡና በሚማርክ ያሬዳዊ ዝማሬ ታቦታን ማጀባቸው፤ ብዙ ምእመናን ሥርዓት ባለው (ክርስቲያናዊ በኾነ) አለባበስ አጊጠው በዕልልታና በጭብጨባ እየዘመሩ በበዓሉ መታደማቸው፤ በተለይ እንደ አዲስ አበበባ ባሉ ሰፋፊ ከተሞች ወጣቶች የክብር ምንጣፍ ለታቦታቱ ለመዘርጋት መፋጠናቸው የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡና የሚያስደስቱ የአገልግሎት ክፍሎች ናቸው፡፡

መለዮ ሹራብ ለብሰው ለታቦታቱ የክብር ምንጣፍ ለመዘርጋት ወዝ እስኪወጣቸው ድረስ የሚሽቀዳደሙ ወጣቶች አቤት ሲያስቀኑ! በእውነት በእግዚአብሔር ጥሪ ለመልካም አገልግሎት የተሰማሩ የተዋሕዶ ፍሬዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ወንድሞችና እኅቶች ስንመለከት ‹‹በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤›› /መክብብ ፲፪፥፩/ የሚለው የጠቢቡ ሰሎሞን ምክር በአእምሯችን ድቅን ይላል፤ የወጣቶቹ ርብርብ ምክሩ በተግባር ላይ እንደ ዋለ የሚያመላክት መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ወጣቶቹ የሚያገለግሉት ምንጣፍ በመዘርጋት ብቻ አይደለም፤ በየከተሞች በሚገኙ መንገዶችና ዐደባባዮች በረጅሙ የተዘረጉ ሰንደቅ ዓላማዎችና ጌጣጌጦች፤ በሙዚቃና በሐራ ጥቃ ‹‹መዝሙራት›› የተዋጡ አካባቢዎችን ነጻ ያወጡ መንፈሳውያን የሲዲ ዝማሬዎች በየዓመቱ የሚከናወኑ የወጣቶቹ ተጨማሪ ተልእኮዎች ናቸው፡፡

img_0524

ታቦታትን አጅበው ለሚጓዙ፣ በፀሐይ ለደከሙ ምእመናን ጠበል ጸሪቅ እና የሚጠጣ ውኀ በየመንገዱ ማቅረብም ሌላኛው ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህ መልካምና አርአያነት ያለው የወጣቶቹ ተልእኮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከትን አካላት ዅሉ ወጣቶቹን በገንዝብ፣ በጕልበት፣ በሐሳብና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ መደገፍና መከባከብ ይገባናል፡፡ እኛም እንደ ዝግጅት ክፍል እነዚህን ወንድሞችና እኅቶችን ‹‹እግዚአብሔር መጨረሻችሁን ያሳምርላችሁ!›› እንላቸዋለን፡፡ ለታቦተ ሕጉ ምንጣፍ በዘረጉ እጆቻችን የሰው ንብረት እንዳንወስድ፤ የሰው ባል ወይም ሚስት እንዳናቅፍ፤ ሰውን እንዳንደበድብ፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተሸቀዳደምንባቸው እግሮቻችን ወደ ኀጢአት መንገድ እንዳንሔድባቸው፤ ደሃ ወገኖቻችንን እንዳንረግጥባቸው እግዚአብሔር የዅላችንንም መጨረሻ ያሳምርልን፡፡

በቃና ዘገሊላ መድኀኒታችን ክርስቶስ ውኀውን ወደ ወይን ጠጅ በቀየረበት ዕለት የሰርግ ቤቱ አጋፋሪ ወይኑን በቀመሰ ጊዜ እንደ ተደነቀ በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል /ዮሐ.፪፥፱/፡፡ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ ‹‹ጥዒሞ አንከረ ሊቀ ምርፋቅ በረከተ ዘአምላክ ገብረ›› በማለት ይህንኑ ምሥጢር ጠቅሶታል፡፡ የቃናው ወይን ጠጅ የቀመሱትን ዅሉ ያስደነቀበት ምክንያት በክርስቶስ ተአምር የተገኘ ንጹሕ መጠጥ በመኾኑ ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች ከመኾናችን ባሻገር በቅዱስ ሥጋው እና በክቡር ደሙ ቤዛነት ለመንግሥቱ የጠራን ልጆቹ ነን፡፡ ስለዚህ የእኛን መንፈሳዊ ኅበረት፣ ክርስቲያናዊ ፍቅር እና የአምልኮ ሥርዓት የሚመለከቱ ሰዎች ይደነቃሉ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ሥርዓት ግን በበዓላት ላይ ብቻ የሚፈጸም ተግባር መኾን የለበትም፡፡ ክርስትናችንን ከዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየቀኑ መኖር ይጠበቅብናልና፡፡

img_0534

አንድ ጊዜ መንፈሳዊ፤ ሌላ ጊዜ ዓለማዊ በኾነ የተቀላቀለ ሥርዓት ከኖርን ግን እንኳን የውጮቹ ሊደነቁብን የውስጦቹ ወገኖቻችንም በእኛ የማስመሰል ክርስትና ሊደናገሩብን፤ ‹‹እነዚህ እንደዚህ ሲያደርጉ የተመለከትናቸው አይደሉም እንዴ?›› በሚል የጥርጣሬ መንፈስም ሊሰናከሉብን ይችላሉ፡፡ ለሌሎች መሰናክል ከመኾን ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገታችን ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም እንደሚሻለን ደግሞ ጌታችን በወንጌል ተናግሯል /ማቴ.፲፰፥፮/፡፡ ጌታችን እንደ ተነናገረው ምግባራችን ለእኛም ለሌሎችም የማይጠቅም ኢ ክርስቲያናዊ ከኾነ እንደ አጥፍቶ ጠፊ ሞቶ መግደል መገለጫችን ይኾናል ማለት ነው፡፡ እናም ራሳችንን አጥተን ለሰዎችም መጥፋት ምክንያት እንዳንኾን እንጠንቀቅ መልእክታችን ነው፡፡

ከዚህ ላይ ይህን ሐሳብ ያነሣነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እንደ በዓለ ጥምቀት ባሉ ልዩ በዓላት ወቅት በየከተማው የሚስተዋሉ ኢ ክርስቲያናዊ ተግባራት እንዲስተካከሉ ለመሳሰብ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጠቆም ያህል በዓሉን ተገቢ ላልኾነ የተቃራኒ ጾታ መቀጣጠሪያ ማድረግ፤ በየመጠጥ ቤቱ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት፣ በጩኸትና በሁካታ አካባቢን እየረበሹ መጠጥ መጠጣትና መስከር እኛንም ሃይማኖታችንንም የሚያስነቅፍ ድርጊት ነውና እናስብበት፡፡ መጠጥ ቢያምረን እንኳን ከዘመዶቻችን ጋር ኾነን በቤታችን ተሰባስበን፣ ጸሎት አድርገን፣ በሥርዓትና በአግባቡ መጠጣት እንችላለን፡፡ በክርስትናችን መስከር (አብዝቶ መጠጣት) እንጂ አልኮል መቅመስ አልተከለከለምና፡፡ ሲበዛና ከሥርዓት ውጪ ሲኾን ግን እንሰክርና በኀጢአት ላይ ኀጢአት ለመፈጸም እንገፋፋለን፡፡ ይህም በቅጣት ላይ ቅጣትን ያመጣብናል፡፡

ttt

በበዓላት ወቅት ለሥጋዊ ጉዳይ የምንቀሽዳድም ክርስቲያኖች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ይህም ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ መንፈሳውያን በዓላትን ከዓለማዊ ግብር ለይተን ልናይ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በዓሉን ስናከብር ለጥላቻ፣ ለድብድብ፣ ለግብረ ዝሙትና ለመሳሰለው ኀጢአት የምንገዛ ወገኖች ይህ የክርስቲያኖች መገለጫ አይደለምና ከዚህ ልማድ እንቈጠብ፡፡ ይህ ልማድ በበዓላት ወቅት በተለይ በበዓለ ጥምቀት ጎልቶ ስለሚታይ በዚህ ዝግጅት አነሣነው እንጂ በሌላ ጊዜ ኀጢአት መሥራት ይቻላል ለማለት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እንደ ጠቀስነው በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ መኖር የዅልጊዜ ተግባራችን ሊኾን የግድ ነውና፡፡ በእርግጥ ተሳስተን ልንሰናከል እንችላለን፤ በዕቅድና በዓላማ ለስካርና ለሌችም የኀጢአት ዘሮች ተገዢ መኾን ግን ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡

img_0574

ከዚሁ ዅሉ ጋርም በየመንገዱና በየዐደባባዩ የምናስቀምጣቸው ቅዱሳት ሥዕላት ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ሊታይ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሥዕላቱ ንዋያተ ቅድሳት እንደ መኾናቸው ለአምልኮ እና ለጸሎት በተመረጠ ልዩና ንጹሕ ቦታ መቀመጥ ሲገባቸው ለፀሐይ፣ ለአቧራና ለነፋስ በሚጋለጡባቸውና በሚቀደዱባቸው መንገዶች ላይ፣ ጭራሽ በቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች በዘፈቀደ መቀመጣቸው ተገቢ አይደለም፡፡ በአንዳንድ የአዲስ አበባ መንገዶች ስንዘዋወር ሥዕላቱ ከተቀመጡበት ቦታ የሚያነሣቸው ጠፍቶ በነፋስ ተቀዳደው ሲወድቁ ዅሉ ተመልክተናል፡፡ የተወደዳችሁ ምእመናን በተለይ ወጣት ክርስቲያኖች ሆይ! ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

img_0575

ከዚህ ላይ የወጣቶቹን ተልእኮ እየነቀፍን እንዳልኾነ ግን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ እርግጥ ነው፤ ወጣቶቹ ይህን የሚያደርጉት ለተንኮል ሳይኾን ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቀናዒነትና በዓሉ ድምቀት እንዲኖረው ከማሰባቸው የተነሣ መኾኑ አይካድም፡፡ ዳሩ ግን ጥሩ የሠራን መስሎን የምናከናውናቸው ተግባራት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተቃርኖ እንዳይኖራቸው፤ እንደዚሁም ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንደሚባለው ለበረከት ያልነው ተልእኮ ለጥፋት እንዳይዳርገን የሥዕላቱን ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ከማስገምገም ጀምሮ እስከምናስቀምጥበት ቦታ ድረስ ከአባቶች ጋር መመካከርና መመርያ መቀበል ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም በየመንገዱ የምንከፍታቸው ዝማሬያት ያሬዳዊነትም አብሮ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ በአጭሩ ቅዱሳት ሥዕላቱን በየመንገዱ ከማስቀመጣችን በፊት (አስፈላጊነቱ በአባቶች ከታመነበት) ሥዕላቱን ከምንመርጥበት መሥፈርትና ከምናስቀምጥበት ቦታ ጀምሮ እስከ አቀማመጠጥ ሥርዓቱ ድረስ፤ እንደዚሁም ከምንከፍታቸው መዝሙራት ያሬዳዊነት አኳያ ዅሉም በሥርዓት ይኾን ዘንድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን አንርሳ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ችግር የለባትም፡፡ የትኞቹን ሥዕላትና መዝሙራትን መጠቀም እንደሚገባን ጠጋ ብለን መምህራንን ብንጠይቅ በቂ ትምህርት ይሰጡናል፡፡

img_0570

እንደሚታወቀው በዓለ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ አገራዊ ሀብታችን ስለኾነ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ሊገኝ እንደሚገባው እሙን ነው፡፡ ስለዚህም በዓሉን በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት በቅርስነት ለማስዝገብ ቤተ ክርስቲያናችን ከመንግሥት ጋር በመኾን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዓለ ጥምቀት በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያደርገው በዐደባባይ የሚከበር በዓል መኾኑ ብቻ ሳይኾን የአከባበር ሥርዓቱ መንፈሳዊነትና ውበት ነው፡፡ የታቦታቱ ዑደት፣ የሊቃውንቱና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዝማሬ፣ የምእመናኑ አለባበስና የወጣቶቹ ሱታፌ፣ ከበዓሉ በፊትም ኾነ ከበዓሉ በኋላ የምናደርጋቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዅሉ የበዓሉ አካላት ናቸው፡፡

የእኛ የአከባበር ዅኔታ ነው በዓሉን በዓል የሚያስብለው፡፡ በሥርዓት ካከበርነው በዓለም እንደ ተደነቀ ይቀጥላል፤ መንፈሳዊ ሥርዓቱን ካጎደልን ግን በዓልነቱም ይረሳል፡፡ ስለዚህ በዐቢይነት ከክርስቶስ ጸጋና በረከት እንሳተፍ ዘንድ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዓሉ በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት ይሳካ ዘንድ ለወደፊቱ ዅላችንም ክርስቲያናዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በዓለ ጥምቀትን ለማክበር እንዘጋጅ እያልን ጽፋችንን አጠቃለልን፡፡ በዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ያከናወናቸውን መልካም ተግባራት አሳድገን፤ ያጎደልናቸውን ደግሞ አሻሽለን በዓሉን በመንፈሳዊ ሥርዓት እንድናከብር አምላካችን ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ በሚቀጥለው ዓመት በበዓለ ጥምቀቱ ይሰብስበን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡