‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ባስመረቀበት ዕለት ተገኝተው በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› በማለት ተመራቂዎቹ ወንጌልን ከዳር እስከ ዳር የማዳረስ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ ከመልካም ዛፍ የተገኛችሁ መልካም ፍሬዎች እንደ መኾናችሁ ይህን ፍሬያችሁን እንድታካፍሉ ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላችኋለች›› ያሉት ቅዱስነታቸው ‹‹መብራታችሁ በሰዉ ዅሉ ፊት ይብራ›› የሚለውን የወንጌል ቃል መነሻ አድርገው በከተማ ብቻ ሳይወሰኑ በየገጠሩ በመዘዋወር በአታላዮች የሚወሰዱ ወገኖችን እንዲጠብቁ እና እንዲያስተምሩ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በየገጠሩ አንድ ሰባኬ ወንጌል ጠፍቶ በየከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በአንድ አጥቢያ ከሁለት በላይ መምህራን መመደባቸውን ተችተዋል፡፡

ሴቶች በመንፈሳዊ ኮሌጁ ተምረው በመመረቃቸውና ከፊሎቹም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው መደሰታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ፈለግ ተከትለው በየኮሌጆቹ የሚሰጠውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲከታተሉና ራሳቸውን በቃለ እግዚአብሔር እንዲያጎለብቱ እናቶችና እኅቶችን መክረዋል፡፡

በመጨረሻም ተመራቂዎቹ በሚሠማሩበት ቦታ ዅሉ በስብከተ ወንጌል ተግተው በማገልገል፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደግሞ የሰባክያነ ወንጌልን አገልግሎት በመቈጣጠር፤ ምእመናኑም ከትክክለኞች መምህራን ትክክለኛውን ቃለ ወንጌል በመማር መንፈሳዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ አባቶች ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡

ኮሌጁ ደቀ መዛሙርቱን ያስመረቀው በቀን፣ በማታ በተመላላሽ እና በርቀት መርሐ ግብር፤ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍል፤ በማስተርስ፣ በዲግሪ እና በዲፕሎማ ማዕረግ ነው፡፡ በዕለቱ ተመራቂዎቹ ባለ አምስት አንቀጽ የአገልግሎት ቃል ኪዳናቸውን በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡ ሴቶች እኅቶቻችንም በልዩ ልዩ ማዕረግ የተመረቁ ሲኾን ከእነርሱ መካከል ጥቂቶቹ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ መሸለማቸው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ የኖረና በማፍራት ላይ የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ማእከል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ሰባክያነ ወንጌል መፍለቂያ የኾነው ኮሌጁ ከኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ያፈነገጠ የኑፋቄ ትምህርት ሲያዛምቱ የተገኙ ሰርጎ ገብ ተማሪዎችን ከአሁን በፊት አውግዞ እንደ ለየ፤ ለወደፊትም ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ሳይፋለስ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ሥርዓቱን የጠበቀ ትምህርት የመስጠት ተልእኮዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኮሌጁ የቦርድ ሥራ አመራር ሪፖርት ተገልጿል፡፡