“በሰላም ማሠሪያ፣ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ» (ኤፌ 4፡3)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“በሰላም ማሠሪያ፣ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ» (ኤፌ 4፡3)
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ፡፡ ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ፡፡ (ሮሜ.12፡16) ተብሎ እንደተጻፈ፡- የቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎት፣ ምእመናንን ከማጠንከርና ከማብዛት አንፃር፣ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ መመራት ያለበት በመሆኑ፣ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጐ በመግባባት፣ በፍቅር፣ በስልትና በዕቅድ የሚፈጸም ነው፡፡
«መከሩ ብዙ ሠራተኛው ግን ትንሽ ነው» (ማቴ. 9÷37) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው በዘመናችን ብዙ የሰው ኃይልና ዐቅም የሚጠይቁ የቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን፤ ቅድሚያ የሚሰጠውን እየመረጡ ሥምሪት ማድረግ፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በምታደርጋቸው የቅዱስ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተ ክህነት አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ከፍተኛ ጉባኤያት፣የትኩረት አቅጣጫዎች ይያዛሉ፡፡ ለእነዚህ አቅጣጫዎች ተፈፃሚነትም፣ በመዋቅሯ ውስጥ ያሉ አካላትና ልጆቿ የሆኑት ምእመናን እርስ በርሳቸው በመናበብ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ይደግፋሉ፡፡
ይህ ሆኖ ሲታይ ግን፡- ያለው ውሱን ዐቅምና ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፤ ባለቤት እና ድጋፍ ያጣው አገልግሎት ተከታታይ እንዲኖረው፣ ሥርዓት ያልወጣለት አገልግሎት ሥርዓት እንዲወጣለት ይደረጋል እንጂ፣ «ልባሞች የሆን እየመሰለን» አስታዋሽ ያጣውን ሳናስታውስ ከግል ፍላጐት አንፃር በተጀመረ ነገር ላይ፣ እንደ ምድራዊ ሀብትና ሥልጣን ክርክር የምንፈጥርበት አይደለም፡፡
የ2010 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ከሚያዝያ 24-29 ቀን 2010 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ተልእኮ መሳካት በሚጠቅሙ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳነት ተይዘው ውይይት ከተደረገባቸው ነጥቦች መካከል፡አንዱ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ ጥቂት የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ የግቢ ጉባኤያት ተሳታፊ ነበርን የሚሉ ተማሪዎች፣ ‹‹ከማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ መዋቅር ተለይተን ለብቻችን እንማር›› በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ይገኝበታል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ጉዳዩን በጥልቀት ከተወያየበት በኋላ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት በሚጠቅም መልኩ‹‹ጥያቄዎቹ የተነሱባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው አህጉረ ስብከት ኃላፊነትን ወስደው፣ ጥያቄ ያቀረቡ ተማሪዎችን በሰንበት ት/ቤት ውስጥ ለብቻቸው እንዲማሩ ይደረግ››ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ ውሳኔ የማያሻማና ግልጽ ሆኖ ሳለ ቀድሞውኑ ሃይማኖታቸውን በስፋት በመማር በመንፈሳዊነታቸው ከመበልጸግ ይልቅ ማኅበሩን በሐሰት በመክሰስ ጉዳዩን አጀንዳ እንዲሆን ያደረጉት ጥቂት ግለሰቦች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በዚህ መልኩ መሆኑ አላስደሰታቸውም፡፡ በመሆኑም ውሳኔውን በማዛባት እና የተለያየ መልክ በመስጠት በተለያዩ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ማናፈስ በመጀመራቸው የውሳኔውን ትክክለኛ ጭብጥ ማብራራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
1ኛ) ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ሁሉንም የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ የግቢ ጉባኤያት አባላትን የማይወክሉ ጥቂቶች ቢሆኑም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹አንዲት ነፍስም ብትሆን እንዳትጠፋ›› በሚል የቤተክርስቲያንን መርህ መሠረት በማድረግ፣ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ መወያየቱን ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ተቀብሎታል፡፡
2ኛ) ማኅበረ ቅዱሳን በአፋን ኦሮሞም ሆነ በሌሎች አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቋንቋዎች የፈጸመው አገልግሎት በቂ እንዳልሆነ አበክሮ ይረዳል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቹ ‹‹ማኅበሩ በአፋን ኦሮሞ በብቃት አገልግሎት አልሰጠንም›› ሲሉ ያቀረቡት ቅሬታ አገልግሎቱ የበለጠ ሊጠናከርና ሊሰፋ ይገባል በሚለው መልኩ ከታየ አግባብነት ያለው ነው ብሎ መቀበል ይቻላል፡፡ነገር ግን በአንጻሩ የማኅበሩን ማንነት እና ዓላማ በማይወክሉ ክሶች፣ ለምሳሌ ‹‹በቋንቋችን እንዳንማር በደል አድርሶብናል፤ ዐሥራት በኲራት ይሰበስባል፤ በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ያስፈራራናል ወዘተ›› (ለብፁዓን አበው የቀረበ ክስ) በማለት መወቀሱን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ እነዚህንና መሰል አሉባልታዎችን በማስወራት ማኅበሩን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባለት በከሰሱበት ወቅት ማኅበሩም ለቀረቡበት ክሶች ምላሹን እንዲሰጥ ዕድል መሰጠት የነበረበት ቢሆንም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶቻችን ይህንን ያላደረጉት ማኅበሩ በእነዚህ መሰል ጉዳዮች ውስጥ እጁን እንደማያስገባ ስለሚያውቁ እና በማኅበሩ አሠራርና መርሖች ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለብቻቸው መማር የፈለጉ ተማሪዎች በሀገረ ስብከት አማካኝነት ይማሩ በማለት ወስነዋል፡፡
3ኛ) የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በማጣመም ወይንም በተሳሳተ መንገድ ባለማወቅ በመተርጎም በአፈጻጸም ሂደት ውስጥ ችግር እንዳያጋጥም ከዚህ በታች የተገለጹት ነጥቦች በአንክሮ ሊታዮ ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡
ሀ) የግንቦቱ ርክበ ካህናት ውሳኔ ‹‹በሲኖዶስ ደረጃ›› ከመሆኑ በቀር ቀድሞውንም ቢሆን በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ተመሳሳይ ውሳኔዎች እና ተሞክሮዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፡- በጅማ፣ በወለጋ እና በቡሌ ሆራ ከየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በተደረጉ ውይይቶች፣ ቋንቋን መሠረት በማድረግ ‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ሥር መሆን አንፈልግም›› ያሉትን በጣም ጥቂት የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ተማሪዎች ‹‹የግድ ማኅበረ ቅዱሳን ሥር ካልሆናችሁ ከቤተ ክርስቲያን ውጡ›› ሊባል እንደማይገባ ግልጽ ስለሆነና የቅድስት ቤተክርስቲያን ጠባይ ባለመሆኑ ለጠያቂዎቹ የተሰጠው ምላሽ ‹‹በአህጉረ ስብከቱ ቀጥተኛ ክትትል ለጊዜው በአጥቢያዎቹ ሥር ሆናችሁ ተማሩ›› የሚል ውሳኔ ነበር፤ ምንም እንኳን አፈጻጸሙ ላይ ግጭቶች ቢስተዋሉም በዚያው አግባብ ለጥቂት ወራት ለማስኬድ ተሞክሯል፡፡ እናም ይህ ውሳኔና የቀደሙ ልምዶች ‹‹የማኅበረ ቅዱሳንን የቤተክርስቲያን አገልግሎት የጎዳ አዲስ ውሳኔ›› ተደርጎ መታየት ስለማይገባ የአህጉረ ስብከት መዋቅራት፣ የግቢ ጉባኤ አገልጋዮችና የማዕከላት አስተባባሪዎች አገልግሎታቸውን አጠናክረውና የጎደለውን ሞልተው ሊቀጥሉበት ይገባል፡፡
ለ) የግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደግሞ ‹‹ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ወጣቶቹን ተረክበው፣ መርሐ ግብር አዘጋጅተው፣ መምህራንን መድበው እንዲማሩ እንዲያደርጉ›› የሚል መሠረታዊ ነጥብ አስቀምጧል፡፡ (የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ) ይህም የሚያመለክተው ከዚህ በኋላ ‹‹በማኅበሩ መዋቅር ውስጥ መገልገል አንፈልግም›› ያሉት የተወሰኑ ተማሪዎች ለሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ከአጥቢያም በላይ ሀገረ ስብከት ቀጥተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አጽንዖት የሰጠ ውሳኔ ነው፡፡ አህጉረ ስብከቶቹ ስንቸገርበት የቆየነውን የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ በቀጥታ መከታተላቸው ደግሞ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የግቢ ጉባኤ ሐዋርያዊ አገልግሎት መቀላጠፍ ምቹ አጋጣሚን የፈጠረ ከመሆኑም በተጨማሪ ከዚህ በተሻለ ትጋት እንድናገለግል ክፍተቶቻችንን ለመለየት ረድቶናል፡፡ በተጨማሪም ‹‹አህጉረ ስብከቱ ይረከቧቸው፣ መምህራንን መድበው ያስተምሯቸው›› ተባለ እንጂ ‹‹ሌላ ግቢ ጉባኤ ይመስርቱ›› ስላልተባለ ይህ ውሳኔ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትም ሆነ ለማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ክርስቲያናዊ አንድነትና የፍቅር አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ያለው ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ሐ) ውሳኔው የፈጠረው መልካም ዕድል ፍሬ እንዳያፈራ ለማድረግ ከዚህ ቀደም ከልምድ እንደታየው መንፈሳዊ ሥነ ምግባራት ከጎደላቸው ጥቂት ወጣቶች በአፈጻጸም ላይ ችግር በመፍጠር አገልግሎቱን ሊያውኩ እንደሚችሉ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በአጥቢያ ሥር የሚገኙትን የግቢ ጉባኤ ቦታዎች እና ንብረቶች ‹‹ይገባኛል›› ሊሉ ስለሚችሉ፤ አላስፈላጊ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እስካሁን በነበረው አካሄድ ‹‹በመንፈሳዊ መንገድ ለመፍታት፣ ቅዱስ ሲኖዶስም የመጨረሻውን ውሳኔ እስኪሰጥ›› በሚል ሁሉንም ነገር ለእነዚያ ወጣቶች ተውላቸው እያልን ግቢ ጉባኤያቱን ስንጫን ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሁለቱም በየመዋቅሮቻቸው ሥር ሆነው እንዲማሩ ተወስኗልና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች መብታቸው እየተገፈፈ እንዲቀጥል ዕድል መስጠት እንደማይገባ ማኅበሩ ያምናል፡፡
በመሆኑም በማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት መሳተፍ ‹‹አንፈልግም›› ብለው ከወጡ እና በሀገረ ስብከቱ እንዲማሩ በቅዱስ ሲኖስ ከተወሰነ በኋላ ከግቢ ጉባኤው ጋር የማይስማሙ ከሆነ ግን በየደረጃው ላሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እንዲሁም ለክልሉ መንግሥትና የጸጥታ አካላት ማሳወቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት አካላት አሳውቀን ጉዳዩ ሳይፈታ በቸልታ ከታለፈ በተለያዩ የአስተደዳር ደረጃዎች ለሚገኙ አካላት ሁሉ ከወዲሁ አጥብቆ ማሳሰብ ይገባል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራትም ይህንኑ አቋም በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት አካላት በአጽንዖት በማሳወቅ አገልግሎቱን ከማይገባ ሥነ ምግባር ከጎደለው ነገር የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡
መ) ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከላይ የተገለጸው ለብቻችን የሚል የመለየት አጀንዳ ይዘው ለሚገኙ በጣት ለሚቆጠሩ ወጣት ያሉባቸው አህጉረ ስብከት ወረዳ ቤተ ክህነት እና የማኅበሩ ማእከላት ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡- በማኅበሩ የግቢ ጉባኤ መዋቅር ሥር በአፋን ኦሮሞ ለሚማሩት ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ማስተማር እና መከታተል፤ ከሃይማኖታቸው የበለጠ ሌላ አጀንዳ የሚበልጥባቸውን ወጣቶች አግባብነት ባለው የትምህርት መልእክትና ፍቅር በመስጠት ወደ እውነተኛ ክርስቲያናዊ አመለካከት እንዲመለሱ ማድረግ፣ በቋንቋው የምንሰጠውን አገልግሎት ከበፊቱም ይልቅ አጠናክረን በመቀጠል በተሳሳተ የአሉባልታ መረጃ፣ በክርስትና ትምህርት ባለመብሰል በሚፈጠር የመረጃ ትንታኔና ስሜታዊነት፣ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል የሚዘራውን የጥላቻ ቅስቀሳ ተከትለው ከግቢ ጉባኤ መዋቅር የሚወጡ ተማሪዎችን ለመመለስ አትኩሮ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ማእከላቱ በልዩ ሁኔታ ሊሰጧቸው የሚያስቧቸውን አገልግሎቶች ለማሳካት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እና አቅጣጫዎች በተመለከተ ከዋናው ማዕከል የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጋር በቀጥታ እየተገናኙ፣ ችግሮችንና ጥያቄዎችን በፍጥነት በመወያየት መፍትሔ የመስጠት እና የማሰጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ሠ) እነዚህንና መሰል ተግባራትን ስናከናውን ደግሞ፣ ከየአህጉረ ስብከቶቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር መወያየትና መመሪያ እየተቀበሉ መተግበር፣ የቅዱስ ሰኖዶሱን ውሳኔ በተለያየ መንገድ በመተርጎም ወይም ዋጋ ባለመስጠት የራሳቸውን አቅጣጫ የሚከተሉትን ለሚመለከታቸው ሁሉ በፍጥነት ማሳወቅ፤ ከሚመለከታቸው ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አካላትም ጋር ተቀራርቦ መመካከር፣ በአከባቢው ተሰሚነት ካላቸው ኦርቶዶክሳውያን የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ጭምር እየተመካከሩ መሥራት በፍጹም ሊረሳ የማይገባው ነው፡፡ ይህ ሲሆን የግቢ ጉባኤያት ጉዳይ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች የማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ አካላት፣ ምእመናንና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ለሚያስቡ፣ ለሚመኙና ለሚቆሙ ሁሉ ነውና፣ አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው ክርስቲያናዊ የሆነ፣ ከቡድንና ከስሜት፣ ከድብቅ አጀንዳና ፍላጎቶች የጸዳ እውነተኛ መፍትሔ ያመጣል ብለን እናምናለን፡፡
በአጠቃላይም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ ሆኖ በጐቿን የሚጠብቅ እንዲሆን ስንሻና፣ በእያንዳንዳችን ፍላጐትና ጥበብ ሳይሆን፣ በፍጹም መንፈሳዊነት መሆን ያለበት ስለሆነ፤ የሚፈጸሙ ተግባራት ሁሉ «ሰላምን ማሠሪያ የሚያደርጉ፣ የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ የሚረዱ እንጂ፣ ተቃራኒ የሆነ ውጤት ለማምጣት ምክንያትና ምቹ ሁኔታ የማይሆኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡» ኤፌ. 4÷3 ለዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትእዛዛተ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ ሁኔታ ይፈጸም ዘንድ፣ የተጣመመውን እያቀኑ፣ የጐደለውን እየሞሉ መሄድ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም እንደ ባለቤት ሆነን በትጋት መከታተል፤ ከቅድስት ቤተክርስቲያን መዋቅር ማለትም ከአህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ አባቶች፣ ምእመናን፣ ሰንበት ት/ቤቶች እና ግቢ ጉባኤያት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅ ነውና፤ በሰላም ማሠሪያነት በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ የሚያግዙና የሚረዱ ነገሮችን ትኩረት ሰጥተን እንሥራ በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
ምንጭ ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቊጥር ግንቦት 2010ዓ.ም ቁጥር1