ቅዱስ ሩፋኤል መልአከ ሰላም ወጥዒና

ጳጕሜን ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ዮሴፍ ይኵኖአምላክ

Kidus Rufael

ጳጕሜን ‹‹ጭማሪ፣ ተውሳክ፣ አምስት ቀን ከሩብ›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ወርኀ ጳጕሜን ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የዓለማችን ባለ ፲፫ ወራት አገር እንድትኾን ያስቻለች ልዩ ወር ናት፡፡

ጳጕሜን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በዚህ የተነሣ በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ወርኀ ጳጕሜን በጾምና በጸሎት /በሱባዔ/ ያሳልፏታል፡፡ በተለይም እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት /ተርኅዎ ሰማይ/ መኾኑን በማመን ምእመናን ወደ ወንዞች በመሔድ እንዲሁም በጳጕሜን ቀናት በሚዘንበው ዝናብ በመጠመቅ በረከትን ይሻሉ፡፡ ጸሎታቸውንም ከምንጊዜውም በበለጠ ያቀርባሉ፡፡

ወርኀ ጳጕሜን የጌታችን ምጽአት የሚታሰብባት በመኾኗ የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነበቡ ምንባባትና ቅዱስ ወንጌሉ እንዲሁም የሚሰበከው ምስባክ ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በወርኀ ጳጕሜን በሚገኘው ሰንበት የሚዘመረው መዝሙርም የሚከተለው ነው፤

‹‹ከመ እንተ መብረቅ ዘይወፅእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ ዐረብ ከማሁ ምጽአቱ ለወልደ እግዚአብሔር ምስለ ኀይለ ሰማያት በንጥረ መባርቅት ምስለ አእላፍ መላእክት ወኲሎሙ ሊቃነ መላእክት አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ ለካህናት፤›› ትርጕሙም፡- ‹‹መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንዲታይ በመባርቅት ፍጥነት ሰማያውያን ኀይላት ከብዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች ጋር በካህናት ራስ ላይ ያሉት አክሊሎች መገኛ የኾነው የሾህ አክሊል ደፍቶ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሁ ይመጣል›› ማለት ነው፡፡

በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡት እና ከሚከበሩት በዓላት መካከል ጳጕሜን ፪ ቀን የሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ በዓለ ዕረፍት፣ ጳጕሜን ፫ ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ሢመት፣ ጳጕሜን ፭ ቀን የነቢዩ አሞጽ በዓለ ዕረፍት ይጠቀሳሉ፡፡

በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከከበሩት ቅዱሳን መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ ‹‹ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል /ጦቢት ፲፪፥፲፭/፡፡

ያለማቋረጥ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት መካከል አንዱ መልአከ ጥዒና ወሰላም /የሰላምና የጤና መልአክ/ የሚባለው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ‹‹ሩፋኤል›› የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡

የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ ‹‹በበሽታ ኹሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል /ሄኖክ ፲፥፲፫/፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› እንዳለ ሄኖክ /ሄኖክ ፮፥፫/፡፡

ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው ለማኅፀን ችግር ኹሉ ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት፣ በማኅፀን እያለ ‹‹ተሥዕሎተ መልክዕ›› (በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በወሊዳቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡

አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል /ጦቢት ፫፥፰-፲፯/፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ‹‹ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሄኖክ ፫፥፭-፯/ ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው /ሄኖክ ፪፥፲፰/፡፡

የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ ‹‹የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው›› /ጦቢት ፲፪፥፲፭/፡፡

የቅዱስ ሩፋኤል በዓሉ የሚከበርባቸው ምክንያቶችም ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም አንደኛው በዓለ ሢመቱን ምክንያት በማድረግ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤቱ ነው፡፡ በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተጻፈው ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ ‹‹እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም!›› ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆመ፤ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፤ ለሕሙማንም ፈውስ ኾነ፡፡ የቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡