ምልጃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ 

በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ዋና ክፍል የተዘጋጀ

 የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

፩. ምልጃ ምንድን ነው?

ምልጃ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሚደረጉ የጸሎት ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምስጋና ጸሎት፣ የልመና ጸሎት፣ የምልጃ ጸሎት አላት፤ እነዚህንም በንባብ፣ በቃልና በዜማ ታደርሳቸዋለች፡፡ ‹‹ጌታ ቅርብ ነው፡፡ በነገር ዂሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› እንዲል (ፊልጵ. ፬፥፮)፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አማላጅ ናት፡፡ በመኾኑም ጸሎተ አስተብቊዖ (የምልጃ ጸሎት) አላት፡፡ ለምሳሌ ያህልም ‹‹ዕውቀትን እርሱን መፍራትንም እግዚአብሔር ይሰጣቸው ዘንድ ስለ መኳንንት እና ሥልጣን ስላላቸው እንማልዳለን›› (ሥርዓተ ቅዳሴ) የሚለው የጸሎት ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነትና መነሻ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ይኸውም ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ዂሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ዂሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ዂሉ እንዲደረጉ ከዂሉ በፊት እንመክራለን›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ካስተማረው ትምህርት የተወሰደ ነው (፩ኛ ጢሞ. ፪፥፩)፡፡

አንድ ክርስቲያን ስለ ራሱ ይለምናል፤ ያመሰግናልም፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ስለ ሌላው ይማልዳል፤ ያመሰግናልም፡፡ በዚህ መልኩ ነው ምልጃና የራስ ልመና ተለያይተው የሚቀመጡት፡፡ ይኹን እንጂ ሁለቱም ያው የጸሎት ዘርፎች ናቸው፡፡ ሁለቱም የጸሎት ክፍሎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሲኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምልጃንና ልመናን ሳትቀላቅል ነው የምታከናውናቸው፡፡ ስለዚህ ምልጃ ማለት ማስታረቅ፣ ማቅረብ፣ ማስማማት፣ ማስማር ማለት ነው፡፡

ምልጃን አስመልክቶ በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ፤

  • አንዳንዶች ‹‹ምልጃ የሚባል የለም፤ ማንም ስለ ማንም አይማልድም፤ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይቻላል›› ይላሉ፡፡
  • አንዳንዶቹ ደግም ‹‹ምልጃ አለ፤ ያስፈልጋል›› ይሉና አማላጁ ግን (ሎቱ ስብሐት፤ ክብር ይግባውና) ክርስቶስ ነው ይሉናል፡፡
  • ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ምልጃ አለ፤ ምልጃ የፍጡር ሥራ ነው እንጂ የፈጣሪ ሥራ አይደለም›› ይላሉ፡፡ የእኛ አስተምህሮም መደቡ ከዚህ ነው፡፡

የፕሮቴስታንት እምነት ስለ ቅዱሳን ምልጃ እንደሚከተለው ያስተምራል፤

  • ቅዱስ ብሎ ነገር የለም፤ ዂላችንም (ምእመናን በሙሉ) ቅዱሳን ነን፡፡
  • በሕይወተ ሥጋ እያለን አንዳችን ለአንዳችን ስንጸልይ ብቻ ነው ምልጃ ተፈጸመ የሚባለው፡፡

ይህ አባባል ብቻውን ካየነው ከላይኛው አባባል ጋር ይጣረሳል፡፡ ሁላችንም ቅዱሳን ከሆን አንዳችን ስለአንዳችን የምንጸልይበት ፋይዳ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄም ያስነሣል፡፡

  • በዐፀደ ሥጋ እንጂ በዐፀደ ነፍስ ማንም ስለ ማንም መጸለይ አይችልም የሚል ነው፡፡

፪. ምልጃ የማን ሥራ ነው?

ምልጃ የፍጡራን ሥራ ብቻ ነው፡፡ በምንም ዓይነት የፈጣሪ ሥራ ሊኾን አይችልም፡፡ ከፍጡራንም ቢኾን የሚፈጽሙት ሁለት አካላት ሲኾኑ አንደኛ እግዚአብሔር አከብሮ የፈጠራቸው ቅዱሳን መላእክት፤ በተጋድሎና በቸርነቱ ባለሟልነት፣ ክብርና ጸጋን የሰጣቸው ቅዱሳን ሰዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተለየ ቅድስናዋና ክብሯ ሰፊውን የምልጃ አገልግሎት ትይዛለች፡፡ ምልጃ የኀጢአተኞች ሥራ አይደለም፡፡ ኀጥእ ሰው የራሱን ኀጢአት ለማስተስረይ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ከኀጢአተኞች ኀጢአት እንጂ በረከት ሊወጣ አይችልምና (፩ኛ ሳሙ. ፳፬፥፲፫)፡፡

፫. የምልጃ ዓይነቶችና አፈጻጸማቸው

የምልጃ ዓይነቱ ወይም መደቡ ሁለት ነው፤ አንደኛው በዚህ ዓለም ማለትም በዐፀደ ሥጋ የሚከናወን ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዐፀደ ነፍስ ማለትም በነፍስ ዓለም የሚከናወን ነው፡፡ በአፈጻጸማቸውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ እንደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በሦስት ዋና ዋና መስመሮች ይከናወናሉ፤

አንደኛ በቅዱሳን ክብርና ባለሟልነት (የማማለድ ጸጋ)፤ በአምላከ ቅዱሳን በልዑል እግዚአብሔር ችሮታ ያመነው በደለኛ ወይም ምልጃ ፈላጊ ምእመን ወዶና ፈቅዶ ወደ አማላጁ ቀርቦ የአማላጁን ስም በክብር እየጠራ ምልጃ ሲጠይቅ የሚፈጸም የምልጃ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነን የነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ ‹‹… ከኤልያስም የተቀበለውን መጎናጸፊያ አነሣ፤ ተመልሶ በዮርዳኖስ ዳር ቆመ፡፡ ከኤልያስም በተቀበለው መጎናጸፊያ ውሃውን መታና የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፡፡ ውሃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (፪ኛ ነገ. ፪፥፩-፲፮)፡፡

በዚህ መሠረት እኛ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፡-

  • በአምላከ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ስም እንማጸናለን
  • ወደ አምላካችን አማልዱን ስንል ቅዱሳንን እናስቀድማቸዋለን
  • የቅዱሳንን ስማቸውን ጠርተን ፈጣሪያችንን ስንማጸን እንደ ውኃ ሙላትና እንደ ተራራ የተጋረጠብንን መከራና ችግር ፈተና ዂሉ ይወገድልናል፡፡

‹‹ኢዮሳፍጥም ‹በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?› አለ፡፡ ከባሪያዎቹ አንዱ ‹በኤልያስ እጅ ላይ ውኃ ያፈስ የነበረው የሳፋጥ ልጅ ኤልሳዕ ከዚህ አለ› አለ፤›› (፪ኛ ነገ. ፫፥፲፩)፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ንጉሡ ራሱ እግዚአብሔርን መጠየቅ ይችል ነበር፤ ይህንን ያደረገው ስለ ትሕትናው፣ ቅዱሳንን ስለ ማክበሩ ነው፡፡ ኤልሳዕም በቀጥታ እግዚአብሔርን ጠርቶ ይህን ውኃ ክፈለው ማለት ይችል ነበር፤ ግን የአባቱን የመምህሩን የኤልያስን ክብር ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ራሱን በትሕትና አሳንሶ መምህሩን አስበልጦና አክብሮ በመገኘቱ ነው፡፡

ሁለተኛ የማማለድ ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ቅዱሳኑ ያለ ምልጃ ጠያቂው አቤቱታ ‹‹ማርልኝ›› እያሉ ወደ ፈጣሪያው የሚያቀርቡት የምልጃ አፈጻጸም ነው፡፡  ይህንን ሁለተኛውን የምልጃ መስመር የሚያብራራልን ምሳሌ በኦሪት ዘፀአት ፴፪፥፩-፴፪ ተመዝግቦ የምናገኘው የሙሴ ታሪክ ነው፡፡ እስራኤል የጥጃ ምስል አቁመው ጣዖት በማምለካቸው እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው በቀጥታ ስለ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፡፡ አስራኤል ለምንልን እስከሚሉትም አልጠበቀም፡፡

እንዲህ እያለም ጸለየ፤ ‹‹አቤቱ ቍጣህ፣ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብጽ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለምን ተቃጠለ? … ከመዓትህ ተመለስ፤ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ፡፡ ‹ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይችንም የተናገርኋትን ምድር ዂሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፤ ለዘለዓለምም ይወርሷታል› ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ፡፡›› ሙሴ ይህን ጸሎት አቅርቦ ሲያበቃ ምን ኾነ ብለን ብንጠይቅ ‹‹እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው መዓት ራራ›› ይለናል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡

ልጇ ታሞባት ምሕረት ለመለመን ወደ ክርስቶስ መጥታ የነበረችው ከነዓናዊት ሴትም ልመናዋን እያቀረበች በነበረችበት ወቅት ሐዋርያት ወደ ክርስቶስ ተጠግተው ‹‹… በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት›› ሲሉ ያሳሰቡት (የማለዱት) እርሷ ለምኑልኝ ስላለቻቸው ሳይኾን ባለሟልነታቸው ባሰጣቸው ጸጋና ክብር ተጠቅመው ነው (ማቴ. ፲፭፥፳፩-፳፰)፡፡ እኛም ከቅዱሳን ኋላ ኾነን ብንጮኽ ይህንኑ ነው የሚያደርጉልን፡፡

ሦስተኛ እግዚአብሔር በአማላጁና በሚማለድለት መሃል ገብቶ ሲያዝ የሚፈጸም የምልጃ ዓይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ በቀጥታ ምሕረት መስጠት እየቻለ ‹‹እገሌ ይጸልይልህ›› ብሎ ኀጥኡን መላኩ ስለ ምን ነው ቢሉ የቅዱሳንን ክብርና ባለሟልነት ለመግለጽ ስለ ወደደ ነው፡፡ አንድም እንዲህ ያለውን የመዳኛ መንገድ ማብዛቱ የቸርነቱ ውጤት ነው፡፡ ይህን ለማየት ምሳሌ የሚኾነን ደግሞ የአብርሃም ታሪክ ነው፡፡ የጌራራው ንጉሥ አቤሜሌክ የአብርሃምን ሚስት ከክብር ሊያሳንሳት በወሰዳት ጊዜ የኀጥኡን መጥፋት ሳይኾን ከጥፋቱ ተመልሶ በሕይወት መኖሩን የሚወድ አምላክ ‹‹የሰውየውን (የአብርሃምን) ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና ስለ አንተም ይጸልያል ትድናለህም፤›› ብሎ ሲራራና ኀጥኡን ወደ ጻድቁ ሲመራው እንመለከታለን (ዘፍ. ፳፥፩-፲፰)፡፡

፬. ምልጃ በዐፀደ ነፍስ

‹‹በዐፀደ ሥጋ ያለውን ምልጃ እንቀበላለን፤ በዐፀደ ነፍስ ግን አይደረግም›› ለሚሉ መጽሐፍ ቅዱስ በዐፀደ ነፍስ ስላለው ምልጃ እንደሚከተለው ያስተምረናል፤ ነፍስ ከእግዚአብሔር የተሰጠች ተመልሳም ወደ እግዚአብሔር የምትሔድ፤ እንድናስብ እንድንናገርና ሕያው ኾነን እንድንኖር ያስቻለችን ረቂቅ ፍጥረት ነች (ዘፍ. ፪፥፯፤ መክ. ፲፪፥፯)፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ዂሉን የሚያውቁት፣ ከሞት (የሥጋ ሞት) በኋላ ሕያው የሚኾኑት፣ የምናናግራቸውና የሚያናግሩን በዚህች ነፍስ ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሙታን ሳይኾን የሕያዋን አምላክ መኾኑን የነገረን ለዚሁ ነው (ማቴ. ፳፪፥፴፪)፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሔዱ ቅዱሳን ከዚህ ዓለም ዕረፍታቸው በኋላ በዚህ ዓለም ስለሚኾነው ነገር እግዚአብሔር በገለጠላቸው መጠን እንደሚያውቁ እና እንደሚያማልዱ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡

ለአብነት ያህል የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንመልከት፤

ሀ. ከዚህ ዓለም ከተለየ (ከክርስቶስ ልደት በፊት) አንድ ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ገደማ የሚኾነው ነቢዩ ሙሴ እና ነፍሱና ሥጋው ሳይለያዩ በብሔረ ሕያዋን የሚኖረው ነቢዩ ኤልያስ ሁለቱም በዘመነ ሥጋዌ ከጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በደብረ ታቦር ተገልጠዋል፡፡ ‹‹ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ኾነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፱፥፳፱-፴፪)፡፡

ለ. ቅዱሳን ሰማዕታት ካረፉ በኋላ በዐፀደ ነፍስ ኾነው በዚህ ዓለም ስላለው ኹኔታ እንደሚያውቁና እንደሚጸልዩ በራእየ ዮሐንስ እንደሚከተለው ተገልጧል፤ ‹‹አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ‹ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?› አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው፤›› (ራእ. ፮፥፱-፲፩)፡፡

ሐ. ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው የአብርሃም የባለጸጋው እና የአልዓዛር ታሪክ በአካለ ነፍስ ምልጃና ልመና መኖሩን የሚያስረዳ ነው (ሉቃ. ፲፮፥፲፱)፡፡

መ. ቅዱስ ጴጥሮስ ከሞቱ በኋላ ለምእመናን እንደሚጸልይላቸው የገለጠው ሌላው ምስክር ነው፡፡ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲኾን አውቃለሁና። ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ፤›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው (፪ኛ ጴጥ. ፩፥፲፫-፲፭)፡፡

ማጠቃለያ

በሥጋ የተለዩ፣ በነፍስ ግን ሕያዋን የኾኑ ቅዱሳን በሥጋ ለሞቱት ሰዎች ያማልዳሉ፤ በሥጋ ያልሞቱት ደግሞ በሥጋ ለሞቱት ‹‹አማልዱን›› እያሉ ይጸልያሉ፡፡ ‹‹በዚያ ወራት የወዳጆቼ የጻድቃን ልመናቸው ወደ ሰማይ ወጣች፤ ከዚህ ዓለም በግፍ የፈሰሰ የጻድቁም ደም በመላእክት ጌታ ፊት ተወደደ፡፡ በእነዚህ ወራቶች በሰማይ የሚኖሩ ጻድቃን በአንድ ቃል ኾነው ተባብረው ያመሰግናሉ፤ ለሰው ፈጽመው ይለምናሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፲፪፥፴፫)፡፡ ሙታን ለሕያዋን፣ ሕያዋን ለሙታን ይጸልያሉ ማለትም ይኸው ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡