ልደተ ስምዖን ነቢይ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የካቲት ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ጥር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ‹‹በዓለ ግዝረት›› በሚል ርእስ ባቀረብነው ትምህርታዊ ጽሑፍ ነቢዩ ስምዖን ጌታችንን እንደ ታቀፈውና ከእርግናው እንደ ታደሰ፤ ከክርስቶስ ቤዛነት ጋር የተያያዘ ትንቢት እንደ ተናገረ፤ ነቢዪት ሐናም የክርስቶስን የማዳን ሥራ ለሕዝቡ ዅሉ እንደ መሰከረች መግለጻችን ይታወሳል፡፡ ኾኖም ግን ይህ ታሪክ የሚነገረው ጌታችን ሥርዓተ ግዝረትን በፈጸመበት ዕለት (ጥር ፮ ቀን) ሳይኾን ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ በገባበት ዕለት (የካቲት ፰ ቀን) መኾኑን እንድትገነዘቡልን በትሕትና እያሳሰብን ወደ ዛሬው ዝግጅታችን እንወስዳችኋለን፤

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የካቲት ፰ ቀን ከሚከበሩ በዓላት መካከል የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት፣ የነቢዩ ስምዖን ልደት (መታደስ) እና የነቢዪት ሐና ዕረፍት በስፋት ይነገራል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን (ጥር ፮ ቀን) በኦሪቱ ሕግ መሠረት ሥርዓተ ግዝረትን ፈጽሟል፡፡ በተወለደ በዐርባኛ ቀኑ (የካቲት ፰ ቀን) ደግሞ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል፡፡ (ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ከታኅሣሥ ፳፱ ቀን ጀምረን ስንቈጥር  የካቲት ፰ ዐርባኛው ቀን ነው፡፡)

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተመዘገበው ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ ‹‹የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ (የበኵር ልጅ) ዅሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ጠባቂዋ ጻድቁ ዮሴፍ ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሳትን ይዘው ጌታችንን በዚህች ዕለት ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ‹‹ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ›› ሲልም በሌሎች ሴቶች ልማድ ለመናገር ነው እንጂ በእመቤታችንስ ይህ ዅሉ ጣጣ የለባትም፡፡ ከሴቶች ተለይታ የተመረጠች ቅድስት የአምላክ እናት እንደ መኾኗ ለድንግል ማርያም ርስሐት በፍጹም አይስማማትም፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ›› ማለት ከሰው የሚለዩበትን ጊዜ ያመለክታል፡፡ ወንዶች በተወለዱ በዐርባ፣ ሴቶች በሰማንያ ቀናቸው ከሰው ይለያሉና፡፡

ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ በሔደ ጊዜም አረጋዊው ነቢዩ ስምዖን ታቅፎት ሰውነቱ ታድሷል፡፡ ይህ ዕለት (የካቲት ፰ ቀን) ‹‹ልደተ ስምዖን›› እየተባለ የሚጠራውም ዕለቱ ነቢዩ ጌታችንን ታቅፎ ከእርግናው (ሽምግልናው) የታደሰበት፤ ከደዌው የተፈወሰበት፤ አምላኩን በሥጋ ያየበት በአጠቃላይ ዳግም የተወለደበት ዕለት በመኾኑ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ስምዖን›› በሚለው ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን መካከል ነቢዩ ስምዖን አንዱ ነው፡፡ የነቢዩን ታሪክ ለማስታዎስ ያህል አባታችን አዳም በተፈጠረ በአምስት ሺሕ ሁለት መቶ ዓመት በንጉሥ በጥሊሞስ ዘመነ መንግሥት የኦሪት መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ እንዲተረጕሙ ከታዘዙ ሰብዓ ሰዎች (ሊቃናት) መካከል አንዱ ነቢዩ ስምዖን ነው፡፡

ይህ ነቢይ ትንቢተ ኢሳይያስ ደረሰውና እየተረጐመ ሳለ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፡፡ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች፤›› ከሚለው ኀይለ ቃል በደረሰ ጊዜ በቀጥታ ቢተረጕመው ንጉሡ እንደማይቀበለው በማሰቡ፤ እርሱም ‹‹ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› ብሎ በመጠራጠሩ ‹‹ድንግል›› የሚለውን ቃል ‹‹ወለት›› (ሴት ልጅ) ብሎ ተረጐመው፡፡ ተኝቶ በነቃ ጊዜም ‹‹ወለት›› የሚለው ቃል ተፍቆ ‹‹ድንግል›› ተብሎ ተጽፎ አገኘና እርሱም ‹‹ድንግል››ን ፍቆ ‹‹ወለት›› ብሎ ይጽፋል፡፡ ዳግመኛም ለሁለተኛና ጊዜ ተኝቶ ሲነቃ ቃሉ እንደ ነበረ ኾኖ ያገኘዋል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ቃሉን እፍቃለሁ ሲልም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ‹‹የተጠራጠርኸውን፣ ከድንግል የሚወለደው ክርስቶስን እስከምታየውና እስከምትታቀፈው ድረስ ሞትን አትቀምስም፤›› ብሎታል፡፡

‹‹መሲሑን ሳታይ አትሞት›› የተባለው ነቢዩ ስምዖን አርጅቶ ከአልጋ ተጣብቆ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ከኖረ በኋላ ትንቢቱ ተፈጽሞ፣ ዘመኑ ደርሶ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በዐርባኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ እስከ በገባበት ዕለት መንፈስ ቅዱስ አነሳሥቶ ወደ ምኵራብ ወሰደው፡፡ በዚያም ጌታችንን ከእመቤታችን ተቀብሎ ለመታቀፍ ታድሏል፡፡ ‹‹የምትጠብቀው ሕፃን ይህ ነው›› ብሎ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነገረው ጊዜም ታውረው የነበሩ ዓይኖቹ ተገልጠዋል፤ ሰውነቱም ታደሷል፡፡

ነቢዩም የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኑ በማየቱ፣ ከደዌው በመፈወሱ እና ከእርጅናው በመታደሱ በአጠቃላይ በተደረገለት ድንቅ ተአምር ዅሉ በመደሰቱ እግዚአብሔርን አመስግኗል፡፡ ‹‹አቤቱ ባሪያህን ዛሬ አሰናብተኝ፤ ዓይኖቼ ትድግናህን አይተዋልና፤›› በሚለው ትንቢታዊ መዝሙሩም ‹‹የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኔ ስላየሁ እንግዲህስ ልረፍ›› በማለት ሞቱን ተማጽኗል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም የክርስቶስን የዓለም ቤዛነትና ክርስቶስ በሥጋው በሚቀበለው መከራ እመቤታችን መራራ ኀዘን እንደሚደርስባት፤ እንደዚሁም ጌታችን ለሚያምኑበት ድኅነትን፣ ለሚክዱት ደግሞ ሞትን የሚያመጣ አምላክ እንደ ኾነ የሚያስገነዝብ ትንቢት ተናግሯል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለነቢዩ ስምዖን የተደረገለትን ታላቅ ሥራ ሲያደንቁ እንዲህ ይገልጹታል፤ ‹‹ሰላም እብል እንዘ እዌድሶ ወእንዕዶ፤ መዝሙረ ማኅሌት በአስተዋድዶ፤ ክብረ ስምዖን ነቢይ ለክብረ ሱራፌል ዘይፈደፍዶ፤ እስመ ሐቀፈ መለኮተ ወገሠሠ ነዶ፤ እኤምኅ ሕፅኖ ወእስዕም እዶ፤ የማኅሌት መዝሙርን በማዘጋጀት እያከበርሁትና እያደነቅሁት ከሱራፌል ክብር ለሚበልጠው ለስምዖን ክብር ሰላም እላለሁ፡፡ እርሱ መለኮትን በእጁ ታቅፏል፤ እሳቱንም ዳሷልና እቅፎቹን እጅ እነሳለሁ፤ እጆቹንም እስማለሁ፤›› /መጽሐፈ ስንክሳር፣ የየካቲት ፰ ቀን አርኬ/፡፡ የዚህ አርኬ መልእክት ኪሩቤል፣ ሱራፌል (ሰማያውያን መላእክት) በእጃቸው የማይነኩት፣ ከግርማው የተነሣ የሚንቀጠቀጡለት፣ እሳተ መለኮቱ የሚቃጥል እግዚአብሔር ወልድን ነቢዩ ስምዖን በክንዱ ለመታቀፍ በመታደሉ ክብሩ ከመላእክት እንደሚበልጥ፤ ለክብሩም የጸጋ ምስጋና እና እጅ መንሻ ማቅረብ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የነቢዪት ሐና ዕፍትም በዛሬው ዕለት ይታሰባል፡፡ ይህቺ ቅድስት ከአሴር ነገድ የተገኘች ደግ እናት ስትኾን አባቷም ፋኑኤል ይባላል፡፡ ክብረ ንጽሕናዋን ጠብቃ በድንግልና ኾና ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሞላት ባል አግብታ ሰባት ዓመት ከባሏ ጋር ቆይታለች፡፡ ከባሏ ጋር ከተፋታች በኋላ ራሷን ጠብቃ ቀንም ሌትም ከምኵራብ ሳትወጣ በጾም በጸሎት ተወስና በሚቻላት ዅሉ እግዚአብሔርን እያገለገለች ሰማንያ አራት ዓመት ኖራለች፡፡ ይህቺ የአንድ መቶ ስድስት ዓመቷ አረጋዊት ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ በገባበት ዕለት በምኵራብ ተገኝታ አምላኳን በዓይኗ ለማየት በማታደሏ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት እና የዓለም ቤዛነት አመነች፡፡ ለዚህ ቀን ያደረሳትን እግዚአብሔርንም አመሰገነች፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታም የክርስቶስን ሥራ እያደነቀች የሰውን ድኅነት በተስፋ ለሚጠባበቁ ለኢየሩሳሌም ሕዝቦች አዳኝነቱን መሰከረች /ሉቃ.፪፥፴፮-፴፱/፡፡ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ዐርፋለች፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ የካቲት ፰ ቀን፡፡

የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ.፪፥፳፪-፴፱፡፡

ከዚህ ታሪክ ከምንገነዘባቸው በርካታ ቁም ነገሮች መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) አንዱ (ወልድ) ነው፡፡ እንደ አምላክነቱ በዅሉም ቦታ የመላ ነውና መሔድ መምጣት፣ መራብ መጠማት የባሕርዩ አይደለም፡፡ ስለዚህም ‹‹ሔደ፤ መጣ፤ ተራበ፤ ተጠማ፤ ተገረዘ፤ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ወዘተ.›› የመሳሰሉ ለፍጡራን የሚስማሙ ቃላት አይነገሩለትም፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ክርስቶስ መገረዝ፣ መሔድ፣ መምጣት፣ መራብ፣ መጠማት የሚስማማው ሥጋን ለብሷልና የሰውነቱን ሥራ ይፈጽም ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ በተቀመጠው ሕግ መሠረት በተወለደ በስምንተኛው ቀን ለመገረዝ፤ በዐርባኛው ቀን ደግሞ ለመቀደስ (መሥዋዕት ለማቅረብ) ወደ ቤተ መቅደስ ሔዷል፡፡ ከዚህም እርሱ አምላክ ነኝ እና በተአምራቴ የማዳን ሥራዬን ልፈጽም ሳይል ከኀጢአትና ከፈቃደ ሥጋ በስተቀር በሰው ሥርዓት ማደጉን፤ እንደዚሁም የትሕትና ጌታ መኾኑን እንማራለን፡፡ ዛሬም ምእመናን ልጅ ሲወልዱ ወንዶችን በዐርባ፤ ሴቶች ደግሞ በሰማንያ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመውሰድ ክርስትና የሚያስነሡት በዚህ ሥርዓት መሠረት ነው፡፡

ከነቢዩ ስምዖን ታሪክም በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ የማይፈጽመውን የማይናገር፤ የተናገረውንም የማያስቀር የእውነት ባለቤት እንደ ኾነ፤ እንደዚሁም እኛ አይደረግም ያልነው ከባድ የሚመስለን ምሥጢር ጊዜውን ጠብቆ መፈጸሙ እንደማይቀር፤ በተጨማሪም እግዚአብሔር በጥበብ የሚገሥፅ፣ የሚያስተምር የፍቅር አምላክ እንደ ኾነ እንገነዘባለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በሥርዓተ ጋብቻ እስኪወሰኑ ድረስ ወንድሞችም እኅቶችም ክብረ ንፅሕናቸውን ጠብቀው መቆየት እንዳለባቸው፤ ከጋብቻ በኋላ ከሁለቱ ጥንዶች አንዱ በሞት ቢለይ ፈቃደ ሥጋቸውን መግታትና ሰውነታቸውን መቈጣጠር የሚቻላቸው ከኾነ እስከ ምድራዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ ራሳቸውን ጠብቀው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ቢኖሩ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ በበረከት ላይ በረከትን እንደሚታደሉ ከነቢዪት ሐና ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ነው፡፡

በእርግጥ በሞት ወይም በዝሙት ምክንያት ከትዳር አጋሮቻችን ጋር የተለያየን ምእመናን ፈቃደ ሥጋችንን መቋቋም የማይቻለን ከኾነ በሥርዓተ ቍርባን በድጋሜ ጋብቻ መመሥረት እንደምንችል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ እናም በሞት ለተለያዩ ጥንዶች ሁለተኛ ጋብቻ ባይከለከልም ሳያገቡ እንደ ነቢዪት ሐና ራሳቸውን ጠብቀው መኖር ለሚፈልጉ ግን አለማግባት ይቻላል፡፡ ራስን ጠብቆ መኖር በእግዚአብሔር ለተመረጡ ሰዎች እንጂ ለዅላችን አይቻለንምና፡፡ ‹‹… እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ አደለው ጸጋ ይኑር፤ ግብሩ እንዲህ የኾነ አለና፡፡ ገብሩ ሌላ የኾነም አለና፡፡ ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ኾነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላቸዋለሁ፡፡ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና …፤›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ /፩ኛ ቀሮ.፯፥፯-፱/፡፡

ነቢዪት ሐና በድንግልና ከመኖሯ እና ሁለተኛ ባል ካለማግባቷ ባሻገር ዓለማዊ ተድላና ደስታን ንቃ፣ ሰውነቷን ጠብቃ፣ ከምኵራብ ሳትወጣ ሰማንያ ዓመት ሙሉ እግዚአብሔርን ስታገለግል መኖሯ ከእርሷ የምንማረው ሌላኛው ቁም ነገር ነው፡፡ እኛም እንደ ነቢዪቷ ሙሉ ጊዜአችንን ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ባይቻለን እንኳን ከሥጋዊው ሥራችን ጎን ለጎን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሔድን ትምህርተ ወንጌል ብንሰማ፣ ብንጸልይ፣ ብንሰግድ፣ ከምሥጢራት ብንሳተፍ፤ እንደዚሁም ለአቅማችን በሚመጥን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ተልእኮ ብናገለግል የእግዚአብሔር ጸጋ በእኛ ላይ ይበዛል፤ እጥፍ ድርብም ይኾናል፡፡ ከዅሉም በላይ በምድራዊው ሕይወታችን የክርስቶስ ቤተ መቅደስ የኾነውን ሰውነታችንን ከኀጢአት ለይተን፣ ራሳችንን ለጽድቅ ሥራ አስገዝተን፣ በመንፈሳዊ ምግባር ጸንተን፣ ስንበድል ተጸጽተን (ንስሐ ገብተን)፣ ቅዱስ ሥጋውን በልተን፣ ክቡር ደሙን ጠጥተን ብንኖር የማያልፈውን መንግሥቱን ለመውረስ እንበቃለን፡፡

የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የነቢዩ ስምዖን እና የነቢዪት ሐና፣ የሌሎችም ቅዱሳን በረከት ይደርብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡